በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር በቴ ኡርጌሳ ተገደሉ


የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር በቴ ኡርጌሳ ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:23 0:00

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራር አባል እና የፖለቲካ ኦፊሰር በቴ ኡርጌሳ፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ መገደላቸው የአሜሪካ ድምፅ ከቤተሰባቸው አባላት ለማረጋገጥ ችሏል።

በቴ ኡርጌሳ፣ ትላንት ማክሰኞ ከምሽቱ 5፡00 ላይ ዐርፈውበት ከነበረው ሆቴል እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን የግንባሩ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ግለሰቡ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ፣ ሁሉም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

“ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም፣ ግንባሩ የራሱን ተጨማሪ ምርመራ ያደርጋል፤” ብሏል መግለጫው።

በመቂ ከተማ የተወለዱት በቴ ኡርጌሳ፣ በዚያው ከተማ እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል።

ኦነግ ባወጣው መግለጫ፣ “በነቁ እና የኦሮሞ የፖለቲካ እና የባህል ምልክት በሆኑ ግለሰቦች ላይ ከሕግ ፍርድ ውጪ የሚፈጸመው ግድያ፣ ለዓመታት የቀጠለና ኾን ተብሎ ኦሮሞዎችን ዝም ለማሰኘት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚፈጸም ድርጊት ነው፤” ብሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በቴ ኡርጌሳ፥ በመንግሥት ኀይሎች በተያዙ በሰዓታት ውስጥ መገደላቸውን ግንባሩ ማስታወቁን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

የ41 ዓመቱ በቴ ኡርጌሳ፣ “በታጠቁ የመንግሥት ኀይሎች”፣ ትላንት ማክሰኞ ረፋድ ላይ፣ መቂ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ሆቴል መያዛቸውን፣ ከግንባሩ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ መረዳት መቻሉን፣ ኤኤፍፒ በዘገባው ላይ አመልክቷል።

“ከመቂ ከተማ ወጣ ብሎ መሊሳ በተባለ ቦታ ላይ፣ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ሞተው አስከሬናቸው መገኘቱን ከቤተሰባቸው አረጋግጠናል፤” ብሏል የኤኤፍፒ ዘገባ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ክልላዊ እና የፌዴራል መንግሥታት ግድያውን በተመለከተ አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና የተሟላ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል። ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ፣ “ግድያውን የፈጸሙት ተጠያቂ ይደረጉ” ሲሉ፣ በኤክስ ማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ጥሪ አድርገዋል።

በቴ ኡርጌሳ፣ ከአንድ ወር በፊት፣ አንትዋን ጋሊንዶ ከተባለና “አፍሪካን ኢንተለጀንስ” ለተባለ መጽሔት ከሚሠራ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ጋራ ተቀምጠው ባሉበት በመንግሥት ኀይሎች ተይዘው ከቆዩ በኋላ በመቶ ሺሕ ብር ዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል።

ሁለቱም ግለሰቦች፣ “በአገሪቱ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር አሲረዋል፤” የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

XS
SM
MD
LG