በድጋሚ የታደሰ
በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ከ3500 የሚበልጡ ሰዎች በሂፐታይተስ ቫይረሶች የተነሳ እንደሚሞቱ የዓለም የጤና ድርጅት ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ። በሚገድለው ሰው ብዛት ከተላላፊ በሽታዎች ሁለተኛ በሆነው በሂፐታይተስ ሳቢያ የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያስጠነቀቀው የዓለሙ የጤና ተቋም፣ በሽታውን ለመዋጋት ፈጣን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስቧል።
በዚህ ሳምንት ፖርቱጋል ውስጥ ‘በሂፓታይተስ’ በሽታ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ የዓለም የጤና ድርጅት በሽታውን የተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል። ከ187 ሀገሮች የተሰበሰበው አዲስ አሃዛዊ መረጃ እንደጠቆመው በሽታውን በሚያመጡ ቫይረሶች ሳቢያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2019 የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሲሆን፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2022 ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ማሻቀቡ ተዘግቧል።
የዓለም የጤና ድርጅት የኤች አይ ቪ፣ የሄፓታይተስ እና በወሲባዊ ግንኙነት ተላላፊ በሽታዎች ክትትል ኃላፊ ሜግ ዶርቲ ባካሄዱት ጋዜጣዊ ጉባዔ የተላላፊው በሽታዎች ይዞታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በጉበት በሽታ ሳቢያ በየቀኑ ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ 83 ከመቶው በሄፐታይተስ "ቢ" በተባለው የበሽታ አይነት ሲሆን፣ 17 ከመቶው ደግሞ በሄፓታይተስ "ሲ" የተነሳ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለማከም በርካሽ ዋጋ የሚገኙ ፍቱን መድሃኒቶች ቢኖሩም በ2022 በሄፓታይተስ "ቢ" በጽኑ ከታመሙ ሰዎች ውስጥ ህክምናውን ያገኙት ሦስት ከመቶ ብቻ መሆናቸውን ሪፖርቱ አክሏል።
በዓለም ዙሪያ ካሉት ለሄፓታይተስ ቫይረስ የተጋለጡ ህሙማን ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ኢትዮጵያ፥ ናይጄሪያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ባንግላዴሽ፣ ሩስያ እና ቪየትናም መሆናቸውንም ሪፖርቱ አውስቷል።
‘ለሄፓይታተስ ቢ’ አዲስ ከሚጋለጡ ሕሙማን መካከል 63 ከመቶው አፍሪካ ውስጥ መሆናቸውን ያመለከተው ሪፖርት፤ በአህጉሪቱ እንደተወለዱ መከላከያ ክትባቱን የሚከተቡት ከአምስት ህጻናት አንድ ብቻ መሆኑን አመልክቷል።
በዓለም ዙሪያ ለሞት በሚዳርገው ሰው ቁጥር ሄፓታይተስ "ቢ" ን በጥቂት ቁጥር የሚበልጠው ቲዩበርክሎሲስ ቲቢ ብቻ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ባወጡት መግለጫ ሪፖርቱ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል። አያይዘውም የሂፓታይተስ ቫይረሶች በመከላከል እና የህሙማኑን ሕይወት በማትረፍ ረገድ ብዙ መሻሻል ቢኖርም ተመርምሮ የሚታከመው ሰው ቁጥር ግን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም