በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ፓርላማ ታሪካዊ የተባለውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች አፀደቀ


ፋይል፡ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት፣ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የወደብ ስምምነት ዙሪያ ያደረጉትን ንግግር ሲያዳምጡ - ጥር 2፣ 2024
ፋይል፡ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት፣ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የወደብ ስምምነት ዙሪያ ያደረጉትን ንግግር ሲያዳምጡ - ጥር 2፣ 2024

የሶማሊያ ፓርላማ ቅዳሜ እለት ባካሄደው ምርጫ፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም እንዲችሉ ስልጣን መስጠትን ጨምሮ፣ ሌሎች የሕገ መንግስት ማሻሻያዎችን አፅድቋል።

የሶማሊያ ሁለት ምክርቤቶችን ያካተተው የፌደራል ምክርቤት፣ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ አራት ምዕራፎች ላይ የቀረቡትን ማሻሻያዎች ያፀደቀው ለሳምንታት ከተካሄደ ከባድ ክርክር በኃላ ነው።

የታችኛው ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሼክ አካን ሞሐመድ ኑር ማዶቤ፣ አብዛኛው የምክርቤቱ አባላት ሕገመንግስቱ እንዲሻሻል ድጋፍ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

በፀደቀው ረቂቅ ውስጥ ከተካተቱ ቁልፍ ድንጋጌዎች መካከል፣ ሶማሊያ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚኖራት የሚደነግገው አንቀፅ ሲሆን፣ ለፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾም እና ከስልጣን የማውረድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ማሻሻያ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ እንዲያገኙ የሚጠይቀውን መስፈርት የተካ ነው።

የተሻሻለው ሕገ መንግሥት የመንግሥት አካላትን የሥራ ዘመን ለአምስት ዓመታት የገደበ ሲሆን የክልል ፕሬዚዳንቶችን እንደ መሪ ይጠቅሳቸዋል።

በረቂቅ ሕገ መንግስቱ ላይ ከሃይማኖት ጋር በተገናኘ ቀርቦ የነበሩት ሦስት አንቀፅ ማሻሻያዎች ግን ተጨማሪ ግምገማ እንደሚደረግላቸው፣ የሕገ መንግስቱን ክለሳ የሚከታተለው ኮሚቴ ሊቀመንበር ሁሴን ኢዶው ገልጸዋል።

"በሃይማኖት ድንጋጌዎቹ ዙሪያ ውሳኔ የማሳለፉ ሂደት የተራዘመው፣ አንቀፆቹ ከሶማሊያ ህዝብ መርሆዎች እና እሴቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው" ሲሉ ያብራሩት ኢዶው፣ ጊዜያዊው ሕገ መንግስት ለአስር አመት የሚጠጋ ጊዜ ጥናት ሲደረግበት መቆየቱን እና እ.አ.አ ከ2012 ጀምሮ በስራ ላይ የነበሩ ሦስት ፓርላማዎች የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG