በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 14 የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ታሳሪዎች በሽብር ተከሰሱ


የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 14 የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ታሳሪዎች በሽብር ተከሰሱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:47 0:00

የፌዴራሉ ፓርላማ እና የክልላዊ ምክር ቤቶች አባላትን ጨምሮ፣ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት 14ቱ ተጠርጠሪዎች በሽብር ተከሰሱ። ዛሬ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ 38 ሰዎችም አብረው ተከሰዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ከቀረቡት ተከሳሾች መካከል ናቸው፡፡

ከምክር ቤት አባላት ውጭ፣ በክሱ መዝገብ ላይ ከተዘረዘሩ 52 ተከሳሾች ውስጥ፡- የኢዜማ አመራር አባል የኾኑት ዶር. ጫኔ ከበደ፣ በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል መሪነት ላይ የሚገኙት እስክንድር ነጋ እና ዘመነ ካሴ ይገኙበታል፡፡

ተከሳሾቹ፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ፊት፣ በዐቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸው የክስ ዶሴ በዛሬው ዕለት እንደደረሳቸው፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ የኾኑት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ይኹንና በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ፣ በዛሬው ችሎት በንባብ እንዳልተሰማ የገለጹት አቶ ሰሎሞን፣ ለዚኽም ምክንያቱን አስረድተዋል፡፡

ለተከሳሾቹ የደረሳቸው የደረሳቸው የክስ ጭብጥ፣ ሁሉም ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32፣ 35 እና 38 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3/2 እንደተላለፉ ይገልጻል፡፡

ክሱ በወንጀሉ ዝርዝር ሥር፣ ተከሳሾቹ፥ የአማራ ሕዝብ ‘አገር ተወስዶበታል፤ ርስቱን ተቀምቷል፤ አገር በአማራ ትውፊቶች እና እሳቤ ብቻ አልተዳደረችም፤’ የሚል አቋም በመያዝ፣ የአማራ ርስት ናቸው የሚሏቸውን መሬቶች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስና አገር ‘በአማራ እሳቤ ብቻ መገዛት አለባት’ በሚል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤” በሚል አትቷል፡፡

ለዚኽም “በኀይል ርምጃ የአካባቢ አስተዳደሮችን በመያዝ፣ በሒደት የአማራ ክልል መንግሥትን በኀይል ከሥልጣን በማውረድ የክልሉን ሥልጣን ለመቆጣጠር፣ በመቀጠልም የፌዴራሉን መንግሥት በኀይል ወደ ድርድር ለማምጣት፣ ለመደራደር ፈቃደኛ ካልኾነ በኀይል ርምጃ ለማስወገድ ተስማምተው” ለተግባራዊነቱ በመሥራት ላይ እንደነበሩ በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ተከሳሾቹ፣ የፖለቲካ ርእዮትን በኀይል ለማስፈጸም በማሰብ፣ ከዚህ በፊት በዐቃቤ ሕግ ተከሰው ክርክር ላይ ያሉ ተከሳሾች ያደራጁትን “የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤትን ዓላማ ለማስፈጸም ተደራጅተው በመሥራት ላይ” እንደነበሩም የተመሠረተባቸው ክስ ያትታል፡፡

“ቀድሞ ተደራጅተው የሽብር ድርጊት ሲፈጽሙ ነበር” ካላቸውና በስም “የአማራ ፋኖ አንድነት” ብሎ የጠቀሳቸውን አራት አደረጃጀቶች ለማስቀጠልና ለመምራት ተከሳሾቹ ጥረት ማድረጋቸውም ሲጠቀስ፣ ከአንደኛ ተከሳሽ አቶ ዮሐንስ ቧ ያለው ጀምሮ በክሱ መዝገብ የተካተቱ 52 ተከሳሾች የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች በዝርዝር ሰፍረዋል፡፡

በዛሬው የችሎት ውሎ በአካል ከተገኙት 14 ተከሳሾች ውጭ ያሉ 38 ተከሳሾችን፣ ፖሊስ አፈላልጎ ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰጠቱን፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡

ከተከሳሾቹ መካከል፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዳመለከቱት ኹሉ፣ እየተፈጸመብን ነው ያሉትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመዘርዘር አቤቱታ ማሰማታቸውን ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ ክልከላዎች ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ጋራ የተገናኙ እንደኾኑ ፖሊስ ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ ችሎቱ፣ ከዛሬ በኋላ ክልከላዎቹ እንዲነሡ ማዘዙን አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበርና ጠበቆች በበኩላቸው፣ ተከሳሾቹ የት መቆየት እንዳለባቸው ክርክር ሳናደርግ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው አቤቱታ ሥነ ሥርዓቱን ያልተከተለ በመኾኑ ውድቅ እንዲደረግ ማመልከታቸውን የገለጹት አቶ ሰሎሞን፣ ችሎቱም የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል፤ ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ ለቀጣይ ሳምንት ዐርብ፣ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ክሱን በንባብ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎት መልስ ኾኗል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG