በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ ተገለጸ


በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:58 0:00

የተኩስ ልውውጦችን ሲያስተናግዱ በቆዩት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ውስጥ፣ ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣዬ ከተማ አስተያየት ሰጭዎች፣ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አመልክተዋል፡፡ ለደኅንነታቸው ሲሉ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች የተፈናቀሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በአሳሳቢ ችግር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት፣ የሰላማውያን ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የንብረት ውድመት መድረሱንና ዘረፋ መፈጸሙን አያይዘው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የጠቆሙ አስተያየት ሰጭዎች፣ አልፎ አልፎ ግን የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ አመልክተዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የፌደራል መንግሥቱ መፍትሔ እንዲያፈላልግም ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን መጡ የተባሉ ታጣቂዎች፣ አሁንም በአጣዬ ከተማ የተወሰኑ ቀበሌዎች ውስጥ እንደሚገኙ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከሰሜን ሸዋም ኾነ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አመራሮች መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ የደረሰው የሰላማውያን ሰዎች ግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀል አገራቸውን እንዳሳሰባት፣ አምባሳደር ኧርቪንግ ማሲንጋ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ በዚኹ መልእክታቸው፣ “ለሰላማውያን ሰዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤ ውስብስቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የጸጥታ ችግር በውይይት እንዲፈታ ተነሣሽነት ያስፈልጋል፤” ብለዋል፡፡ የትኛውም ወገን ሰዎችን ከቀዬአቸው የሚያፈናቅል የኀይል ርምጃ መውሰድ እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG