በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ አዲሱ የዙማ ፓርቲ ከምርጫው እንዲታገድ ጠየቀ


የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ (ፎቶ ፍይል፣ ኤፒ)
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ (ፎቶ ፍይል፣ ኤፒ)

የደቡብ አፍሪካው ገዥ ፓርቲ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኤ ኤን ሲ) አዲስ የተቋቋመውን ተፎካካሪ ፓርቲ በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ እንዳይወዳደር ለማሳገድ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል፡፡

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የሚደገፈውና አዲስ የተቋቋመው ተቃዋሚ ፓርቲ uMkhonto weSizwe ወይም በአጭሩ MK (ኤምኬ) ተብሎ ይታወቃል፡፡

አዲሱ ፓርቲ በኔልሰን ማንዴላ የተመሰረተው እና አፓርታይድን የተዋጋ፣ ኋላም ወደ ሰላማዊ ትግል ከተሸጋገረ በኋላ በኤኤንሲ የታገደውንና የተበተነውን “ኤም ኬ” የሚለውን የታጣቂ ክንፍ መጠሪያ ስም በመጠቀም በአዲስ መልክ መደራጀቱም ገዥውን ፓርቲ ኤ ኤን ሲን አስቆጥቷል፡፡

እኤአ ግንቦት 29 የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት የዳሰሳ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

እኤአ በ1994 በዚያች ሀገር የዲሞክራሲ ሥርዓት ከተመሠረተ ወዲህ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ በግንቦቱ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ50 በመቶ ያነሰ ድምጽ እንደሚያገኝ ይገመታል።

ከትላንት በስቲያ ሰኞ ወደ ምርጫ ፍርድ ቤት ያመራው ገዥው ፓርቲ ኤ ኤን ሲ አዲሱ ኤም ኬ (MK) ፓርቲ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በምርጫ ኮሚሽኑ ሲመዘገብ አስፈላጊውን መስፈርት አላሟላም በማለት ተከራክሯል።

የፓርቲውን የወጣቶች ክንፍ መሪ ጨምሮ አንዳንድ የአዲሱ ፓርቲ አባላት በበኩላቸው ፓርቲያቸው በግንቦቱ ምርጫ እንዳይሳተፍ ከተከለከለ ሁከት ሊፈጠር ይችላል ብለው አስፈራርተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG