በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመንግሥት ወጪ ጉዳይ የሪፐብሊካን እና ዲሞክራት ስምምነት


ፎቶ ፋይል፡ የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ፎቶ ፋይል፡ የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ወጪ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሪፐብሊካን እና ዲሞክራት ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ከፍተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲው እና የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪዎች ባለፈው ጥቅምት የጀመረው የመንግሥት በጀት ዓመት እስኪጠናቀቅ የሚበቃ ወጪ እንዲፈቀድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዛሬ ማክሰኞ አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት የፊደራሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚዘጉበት የያዝነው ሳምንት መጨረሻ ቀነ ገደብ ከመድረሱ በፊት የበጀት ሕጉን ለማጽደቅ ጥድፊያው ተጀምሯል።

በጀቱን አስመልክቶ የቀረው አጨቃጫቂ ጉዳይ የአገር ደህንነት ሚኒስቴር በጀት እንደነበረ ተመልክቷል። ከሜክሲኮ ጋራ በሚዋሰነው የዩናይትድ ስቴትስ ድንበር በኩል የሚገቡት ፍልሰተኞች ቁጥር ማሻቀቡ በፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና በቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ መካከል በሚደረገው የምርጫ ፉክክር አቢይ ጉዳይ ሆኗል።

የመንግሥት ወጪን በሚመለከት ስምምነት ላይ መደረሱን ሪፐብሊካኑ የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ማይክ ጆንሰን በህግ መወሰኛው ምክር ቤት የብዙሃኑ ዲሞክራቶች መሪው ሴኔተር ቸክ ሹመር ዛሬ ጠዋት በሰጧቸው መግለጫዎች ይፋ አድርገዋል።

የምክር ቤት አባላቱ ድምጽ ከመስጠታቸው በፊት መዘጋጀት ያለበት የስምምነቱ የጽሁፍ ሰነድ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

ስምምነት የተደረገበት ወጪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከመስከረም 30 በሚዘልቀው የበጀት ዓመት ከሚያስፈልገው ወደ 1 ነጥብ 66 ትሪሊዮን ዶላር ሦስት አራተኛ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ይጠበቃል።

34 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰው የዩናይትድ ስቴትስ የብድር ዕዳ እየጨመረ ሲሆን በምክር ቤት ቀጣይ ጭቅጭቅ እንደሚጠብቅ ተመልክቷል።

ፕሬዚደንት ባይደን እና የተወካዮች ምክር ቤት ሪፐብሊካኖች ለቀጣዩ የበጀት ዓመት ወጪ የየበኩላቸውን ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን ቅድሚያ የሰጧቸው ጉዳዮች በከፍተኛ ድረጃ የተለያዩ መሆናቸውን ዜናው ጨምሮ አውስቷል።

የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጆንሰን የ95 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ጸጥታ ድጋፍ ዕቅዱን ለአባላት ድምጽ ለማቅረብ አሁንም ፈቃደኛ አይደሉም። እቅዱ ተሟጋቾች ለዩክሬይን በአንገብጋቢነት ያስፈልጋታል ያሉትን የገንዘብ እርዳታ ያካተተ ነው።

ወጪውን የመወሰኛ ምክር ቤቱ በሁለቱም ፓርቲዎች አባላት ድጋፍ ያሳለፈው ሲሆን በተወካዮች ምክር ቤቱም የመቅረብ ዕድል ቢያገኝ ጠቀም ያለ የድጋፍ ድምጽ ሊያገኝ እንደሚችል ይጠበቃል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG