በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኒዠር እና የአሜሪካ ትብብር  መቋረጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴውን ስጋት ላይ ጥሏል 


ፎቶ ፋይል - ኤ ሲ -130 የአሜሪካ አየር ኃይል አውሮፕላን ታክሲ ፊት ለፊት ለውድድር የተዘጋጁ ወታደሮች ቆመው/ እአአ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም.
ፎቶ ፋይል - ኤ ሲ -130 የአሜሪካ አየር ኃይል አውሮፕላን ታክሲ ፊት ለፊት ለውድድር የተዘጋጁ ወታደሮች ቆመው/ እአአ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኒዠር ሁንታ ለዓመታት ሀገሪቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ታደርግ የነበረውን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጡን ተከትሎ፣ አሜሪካ በሳህል አካባቢ የምታካሂደውን ፀረ-ሽብር ዘመቻ የወደፊት እጣ ፈንታ ለመገምገም ተጣድፋለች። የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሰሜናዊ ኒዠር በሚገኘው የአየር ኃይል ሠፈር በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ያሰፈረ ሲሆን፣ ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ በሚገኙት እና ከአል-ቃኢዳ እና ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ቁርኝት ያላቸው ኃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው ሰፊ የሳህል ቀጠና በረራዎችን ያካሂዳሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ መልዕክተኛ ሞሊ ፊ፣ ከአሜሪካ የጦር ኃይል የአፍሪካ እዝ አዛዥ ጀነራል ማይክል ላንግሊ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ታጅበው፣ በዚህ ሳምንት በድጋሚ ወደ ኒዠር ዋና ከተማ፣ ኒሜይ ተጉዘዋል። ሞሊ ፊ ባለፈው ታህሣስ ወደኒያሚ ተጉዘው የነበረ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክቶሪያ ኑላንድም ባለፈው ነሃሴ ወደኒዠር ተጉዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ትናንት እሁድ ኤክስ በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መልዕክት፣ ከሁንታው አመራር ጋር ግልፅ ውይይት መደረጉን እና ግንኙነቶች መቀጠላቸውን አስታውቋል። ሆኖም ዩናይትድ ስቴትስ በሀገሪቱ ውስጥ ለመቆየት በሚያስችላት ስምምነት ላይ ለመደራደር መንገድ ይኖራት እንደሆን በግልፅ አልታወቀም።

የኒዠር ሁንታ መሪ ጀነራል አብዱራህማን ቲቺያኒ፣ የሙስሊሞች ቅዱስ የፆም ወር ራማዳን በተጀመረበት ወቅት ወደ ኒጀር የተጓዘውን የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ቡድን ለማግኘት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ኒዠር በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫም ተሰርዟል።

ዋይት ኃውስ በቅርቡ ለአሜሪካ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት እንዳስታወቀው፣ ዩናይትድ ስቴትስ እስካለፈው ታኅሣሥ በነበረው ጊዜ ኒዠር ውስጥ 650 ሠራተኞች ነበሯት።

በኒዠር የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር በሰው እና ሰው አልባ በሆኑ መሣሪያዎች ለሚካሄዱ ስለላዎች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ በሳህል ለሚካሄዱ ተልዕኮዎች የእግረኛ ወታደሮችም ጭምር ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል። ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ2017 በኒዠር በተካሄደ የጋራ ዘመቻ የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ የእግረኛ ወታደራዊ ድጋፎቹ ቀንሰዋል።

ሁንታው ኒዠር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ያላትን ወታደራዊ ትብብር እንዲያቋርጥ ምን እንዳነሳሳው በግልጽ አልታወቀም፡፡ የሁንታው ቃል አቀባይ አማዱ አብዳራማኔ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በሰጡት ቃል “በቅርብ ሳምንታት በኒዠር የአእየር ክልል ላይ የተደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ በረራዎች ህገወጥ ናቸው” ያሉ ሲሆን የኒዠርን ወታደራዊ ገዢዎች በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች የሚረዱት ኒዠራዊ ጋርባ ሳይዱ በበኩላቸው “ ዩናይትድ ስቴትስ ከስትራተጂያዊ አጋሮቿ መካከል እንድትመርጥ ለማስገደድ እየሞከረች ናት” በማለት ነቅፈዋል፡፡ “ከአሁን ወዲያ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮችና ሲቪል ሠራተኞች ኒዠር ምድር ላይ ሊቆዩ አይችሉም”ሲሉም ለአሶሲየትድ ፕሬስ በሰጡት ቃል አክለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ልዑኳ ሞሊ ፊ ከታህሣሱ የኒዠር ጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት ቃል ከሁንታው መሪዎች ጋር “ጥሩ ውይይት አድርገናል” ያሉ ሲሆን ወታደራዊ ትስስር እና ርዳታ እንዲቀጥል ምርጫ የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ እንዲያወጣ ለሁንታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ኒያሜ ከሩስያ ጋራ ግንኙነቷን ከማጠናከር እንድትቆጠብ ዩናይትድ ስቴትስ ማስጠንቀቋን ሞሊ ፊ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG