በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ኅብረት ለግብፅ የ8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገ


የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ጋር በካይሮ የኢቲሃዲያ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት (ፎቶ ፋይል)
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ጋር በካይሮ የኢቲሃዲያ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት (ፎቶ ፋይል)

የአውሮፓ ኅብረት ለግብፅ የ8 ቢሊዮን ዶላር ጥቅል እርዳታ መፍቀዱን ዛሬ እሁድ አስታወቀ።

የጥሬ ገንዘብ ተቸግራለች ለተባለቸው ግብፅ እርዳታው የተፈቀደው በጎረቤት ሀገራት ያለው የኢኮኖሚ ጫና ፣ ግጭት እና ትርምስ ብዙ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች እንዲያመሩ ሊያደርጋቸው ይችላል በሚል ስጋት መሆኑን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ብድሮችን እና ርዳታዎችን የሚያካትተው ስምምነት የሚፈረመው የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፣ የቤልጂየም ፣የጣሊያን ፣ ኦስትሪያ ፣ቆጵሮስ እና ግሪክ መሪዎች ሀገሪቱን በሚጎበኙበት ወቅት መሆኑን የግብፅ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በካይሮ የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ተልእኮ እንደገለጸው ጥቅል የገንዘብ ድጋፉ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በአረቡ ዓለም በቁጥር የላቀ የሕዝብ ብዛት ላላት አገር የሚሰጠውን ዕርዳታ እና ብድር ያካትታል።

በግብፅ ከአውሮፓ ኅብረት ተልዕኮ የተገኘ ሰነድ እንደሚያመለክተው ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ወደ "ስልታዊ እና ሁሉን አቀፍ አጋርነት" ደረጃ በማድረስ የግብፅ እና የአውሮፓ ኅብረትን በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማስፋት መንገድ ይጠርጋል ተብሏል፡፡

በስምምነቱ መሠረት የአውሮፓ ኅብረት የግብፅ መንግስት ድንበሩን እንዲያጠናክር ይደግፋል፡፡ በተለይም በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ፣ ድህነትን እና ግጭቶችን በመሸሽ፣ የሚሰደዱ ፍልሰተኞች ዋና መሸጋገሪያ የሆነችውን የሊቢያንና እንዲሁም ዓመት ካስቆጠረው የሱዳን ተቀናቃኝ ጀኔራሎች ጦርነት እየሸሹ የሚመጡ ሱዳናውያንን ስደተኞች የሚመጡባቸውን ድንበሮች እንዲያጠብቅ ድጋፍ ያደርጋል።

ግብፅ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ከጦርነት ወይም ከድህነት ለማምለጥ ለሚሞክሩ ስደተኞች መሸሸጊያ ሆና ቆይታለች። አደገኛውን የሜዲትራኒያን ባህር በመሻገር ወደ አውሮፓ ለመዝለቅ እንደመተላለፊያ ቦታ ሆና የምታገለግል ስፍራ መሆንዋም ተገልጿል፡፡

በእስራኤል እና በሃማስ ጦርነት የተነሳ በሚፈጠረው የፍልስተኞች ብዛት ግብፅ ከፍተኛ ጫና እየገጠማት ሲሆን ድንበሯ ሊጣስ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ርዳታውን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ግብፅ ባላት የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ትችት ፈጥሯል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስምምነቱን አውግዞ የአውሮፓ መሪዎች በግብፅ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ተባባሪ እንዳይሆኑ አሳስቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG