በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬኒያዊያን የህክምና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ አደረጉ


የኬኒያዊያን ሀኪሞች ተቃውሞ
የኬኒያዊያን ሀኪሞች ተቃውሞ

ኬኒያዊያን የመንግስት ሆስፒታል ሀኪሞች በጎሮጎርሳዊያኑ 2017 ሀኪሞች ያደረጉትን እና ህሙማን ህይወታቸውን ያጡበትን አድማ ተከትሎ መንግስት የገባውን ቃልኪዳን አለማክበሩን በመግለጽ በድጋሚ የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። የኬኒያ የህክምና ፣ የፋርማሲ ባለሞያዎች እና የጥርስ ህክምና ባለሞያዎች ህብረት፤ የኬኒያ መንግስት 1200 የህክምና እጩዎችን ወደ ስራ እስካላስገባ እና ለሀኪሞች ጠቅላላ የጤና መድህን ዋስትና እንስካላረጋገጠ ወደ ስራ ገበታቸው እንደማይመለሱ አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የሰራተኛ ፍርድቤቱ ማኅበሩ አድማውን ለጊዜው እንዲያቆይ ቢጠይቅም 4000 የጤና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። የህክምና ባለሞያዎች ህብረት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሚስከላህ መንግስት ከዚህ በፊት የሰራተኛ ፍርድ ቤቱ ለሦስት ተደጋጋሚ ጊዜያት የሀኪሞች ደሞዝ ከፍ እንዲል እና የታገዱ ሀኪሞች ወደ ህክምና ስራቸው እንዲመለሱ የበየንበትን ተቀብሎ ተግባራዊ ባለማድረጉ፤ አሁን ላይ እነሱም የፍ/ቤቱን ውሳኔ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ በኬኒያ በጽኑ ህክምና ክፍል የሚሰሩ ሀኪሞች ህሙማን ህይወታቸው እንዳያልፍ በስራ ገበታቸው ላይ እንደሚቆዩ ተገልጿል።

ሲቲዝን ከተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉት የህክምና ባለሞያዎች ህብረት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሚስከላህ ሀኪሞች ስራው በሚያስከትለው ጭንቀት እራሳቸውን እያጠፉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ሀኪሞች ሲታመሙ ለመታከም የገንዘብ መዋጮ ይለምናሉ ብለዋል።

የህክምና ባለሞያዎቹ አድማ በመላው ሀገሪቱ የጤና ስርዓት ላይ ተጽዕኖው የታየ ሲሆን ኬኒያዊያን ህሙማን ያለምንም ድጋፍ በመጉላላት ላይ ይገኛሉ።

በኬኒያ ሀኪሞች ከስድስት ዓመት የዩኒቨርስቲ ትምህርት በኋላ ከ400 እስከ 850 ዶላር የወር ክፍያ ብቻ የሚያገኙ ሲሆን፤ ይህ ገቢ በስድስት ወር ስልጠና ጀማሪ የሀገሪቱ የፖሊስ ሰራዊት የሚያገኙት መሆኑ ተገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG