በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፍልስጤማዊያን የረመዳን ጾም በጀመሩበት ዕለት እስራኤል ጥቃት አደረሰች


በራፋህ፣ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ቤታቸው የፈረሰባቸው ፍልስጤማውያን ከፍርስራሹ ውስጥ ንብረታቸውን ሲፈልጉ - መጋቢት 11፣ 2024
በራፋህ፣ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ቤታቸው የፈረሰባቸው ፍልስጤማውያን ከፍርስራሹ ውስጥ ንብረታቸውን ሲፈልጉ - መጋቢት 11፣ 2024

ፍልስጤማውያን የረመዳን ጾም በጀመሩበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ ጥቃቶች ማካሄዷን ዛሬ ሰኞ አስታውቃለች፡፡

ጥቃቱ የቀጠለው እስራኤል እና ታጣቂው ቡድን ሐማስ፣ የረመዳን ጾም ከመግባቱ አስቀድሞ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ግብጽ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኳታር የተሳተፉበት ድርድር ለሳምንታት መካሄዱን ተከትሎ ነው፡፡ ሐማስ የያዛቸውን ታጋቾች እንዲለቅ እና እስራኤልም ያሰረቻቸውን ፍልስጥኤማውያን እንድትፈታ በሚጠይቀው ድርድር ሲሳተፉ የነበሩት የሐማስ ተደራዳሪዎች ባለፈው ሳምንት ከካይሮ ሲወጡ በሰጡት ቃል፣ ድርድሩ በዚህ ሳምንት እንደሚቀጥል ተናግረው ነበር፡፡

የእስራኤል የጦር ኃይል በደቡባዊ ጋዛ፣ በካን ዩኒስ እና በሌሎችም አካባቢዎች እንዲሁም ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በአየርም በየብስም ጥቃት ማካሄዱን ገልጿል፡፡

የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ በእስራኤል ጥቃት ባደረሰችው ጥቃት 67 ሰዎች እንደተገደሉ አመልክቷል፡፡ ጦርነቱ ባለፈው ጥቅምት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 31 ሺህ 112 መድረሱንም አክሎ አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ረሃብ ላይ ላሉ ፍልስጥኤማዊያን ሰብዓዊ እርዳታ ማስገቢያ እንዲሆን ጋዛ ጠረፍ ላይ ጊዜያዊ የጭነት ማራገፊያ ግንባታ የሚጀምር የዩናይትድ ስቴትስ መርከብ ወደ ሜድትሬኒያን ባህር በመጓዝ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጊዜያዊው የጭነት ማራገፊያ የሚቋቋመው ተጨማሪ የምግብ እና የህክምና ቁሳቁስ እርዳታዎች በቅርብ ርቀት ባለችው በቆጵሮስ በኩል ለማድረስ ሲሆን በጭነቶቹ ውስጥ ለሀማስ ታጣቂዎች በድብቅ የጦር መሣሪያ እንዳይላክ በእስራኤል ኃይሎች እየተፈተሸ እንደሚያልፍ ተመልክቷል፡፡

የምግብ እርዳታ የጫነ የስፔይን የበጎ አድራጎት ድርጅት መርከብ በቅርቡ ከቆጵሮስ እንደሚነሳ ተገልጿል፡፡ “ኦፕን አርምስ” (Open Arms) የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት 200 ቶን የምግብ እርዳታ ጭኖ እንደሚጓዝ አስታውቋል፡፡ ወርልድ ሴንትራል ኪችን ( World Central Kitchen) የተባለ የዩናይትድ ስቴትስ የበጎ አድራጎት ተቋምም ጋዛ ጠረፍ ላይ ባለው ጊዜያዊ ማሳረፊያ ጭነቱን እንደሚቀበል ተጠቁሟል፡፡

ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሐማስ እ.አ.አ ጥቅምት 7 ቀን እስራኤል ላይ ያደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ሲሆን በጥቃቱ 1200 ሰዎች መገደላቸውን እና 250 የሚሆኑ መታገታቸውን እስራኤል አስታውቃለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶ ሺዎች የተቆጠሩ ፍልስጥኤማዊያን ረሃብ ላይ መሆናቸውን ገልጾ አስጠንቅቋል፡፡ አያይዞም ከጦርነቱ በፊት ወደጋዛ የምግብ እርዳታ የያዙ 500 የጭነት መኪናዎች በየቀኑ ይገቡ እንደነበር ገልጾ ባለፉት አምስት ወራት ቁጥር ከዚያ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ማዕከላዊ ዕዝ እና የዮርዳኖስ የአየር ኃይል ትናንት በጋራ ሆነው የተዘጋጁ የዕለት ምግቦችን እና ሩዝ ፓስታ እና የታሸጉ ምግቦች የያዙ ጥቅሎች ሰሜን ጋዛ ለሚገኙ ነዋሪዎች ከአየር መጣላቸውን ዜናው ጨምሮ አስታውቋል፡፡ ሆኖም ጋዛ ውስጥ ካለው ችግር አኳያ በቂ አለመሆኑን ባለስልጣናቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አምስት ሰዎች ከአየር የተወረወረ የምግብ እርዳታ ጥቅል መትቷቸው መሞታቸው ተገልጧል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG