የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎች የሲቪሎችን መኖሪያ ቤቶች እና የሕዝብ መገልገያዎች ጥለው ካልወጡ በስተቀር በሱዳን ለረመዳን የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይኖር የሱዳን ጦር ጀነራል እሁድ እለት አስታወቁ።
ጀነራሉ መግለጫውን ያስተላለፉት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት፣ ለሙስሊሞች ቅዱስ ወር ግጭት እንዲቆም ጠይቆ ያሳለፈውን የውሳኔ ሀሳብ ተከትሎ ነው።
ላለፉት አስራ አንድ ወራት ከጦሩ ጋር ሲዋጋ የቆየው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በበኩሉ የተኩስ ማቆም ጥሪውን ተቀብሏል።
ሆኖም ጀነራል ያሲር አል-አታ በመግለጫቸው፣ ጦራቸው በቅርብ ቀናት ከሱዳን ዋና ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኦምዱርማን ያገኘውን የበላይነት ጠቅሰዋል። በሳምንቱ ማጠቃለያም የሱዳን ጦር ወታደሮች በኦምዱርማን፣ ዋድ ኑባዊ መኖሪያ ሰፈር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።
ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ጦሩ በተቀናቃኙ ቡድን ተበልጦ የነበረ ቢሆንም፣ በየካቲት ወር የተወሰነውን የኦምዱርማን ክፍል በመያዝ የመጀመሪያውን ድል አግኝቷል። በከተማዋ የሚገኙ ሁለት የጦር ሰፈሮች ማገናኘት እንደቻለም ገልጿል።
በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው እ.አ.አ በሚያዚያ 2023 ሲሆን እስካሁን ወደ 25 ሚሊየን የሚጠጉ ሱዳናውያንን የሰብዓዊ ርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል። ወደ 8 ሚሊየን የሚጠጉ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል።
መድረክ / ፎረም