በሰሜን ናይጄሪያ የእስልምና አክራሪ ሳይሆን አይቀርም በተባለ ቡድን 50 የሚሆኑ ሰዎች ታግተው ተወስደዋል ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ተናገሩ።
አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው የተባሉ 50 የሚሆኑ ሰዎችን ያገተው በእስልምና አክራሪነት የሚጠረጠር ሽፍታ ቡድን ሳይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል። ላለፉት አስርት ዓመታት ጦርነት ያወጀው ቡድን የጅምላ ጠለፋም ሲያካሂድ ሰንብቷል።
ቦኮ ሃራም እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው የኢስላሚክ ስቴት (አይሲስ) ተገንጣይ ቡድኖች፣ በሰሜን ናይጄሪያ በሚገኘው ቦርኖ ግዛት የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎችን እና ሲቪሎችን ኢላማ በማድረግ፣ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ አፈናቅለዋል።
በዚህ ሣምንት ሰኞ ዕለት የተፈጸመው ጠለፋ፣ ከቻድ እና ከካሜሩን ጋራ በሚዋሰነውና፣ ጋምቦሩ በተሰኘው ጠረፋማ አካባቢ መሆኑን፣ ጂሃዲስቶችን በሚፋለመው እና በሲቪሎች የተቋቋመው የጋራ ግብረ ኃይል ውስጥ ያሉ አንድ ባለሥልጣን አስታውቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት እንዲሰጡ እንዳልተፈቀደላቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሥልጣን እንዳሉት፣ የተጠለፉት 50 የሚሆኑት ሰዎች፣ በተፈናቃይ መጠለያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ናቸው። በጠለፋው ወቅት የማገዶ እንጨት ፍለጋ በቻድ ሓይቅ አቅራቢያ ወደሚገኘው አካባቢ አቅንተው የነበረ ሲሆን፣ በአካባቢውም ሁለቱ አማጺ ቡድኖች እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል።
ዘገባው የሮይተርስ ነው ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።