በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቡርኪናፋሶ  170  ዜጓቿ  በጽንፈኞች ጥቃት  እንደተገደሉ  አስታወቀች።


.
.


በወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ ባለችው ቡርኪናፋሶ የእስላማዊ የጽንፈኛ ኃይሎች ጥቃት ተባብሶ ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት በሶስት መንደሮች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች 170 ሰዎች እንደተገደሉ መንደሮቹ የሚገኙበት ቀጠና ዐቃቢ ህግ አስታወቁ።

ጥቃቱ በተፈጸመበት የአውሮፓዊያኑ የካቲት 25፣ ምስራቃዊ ቡርኪና ውስጥ በሚገኝ መስጊድ እና በሰሜን በሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸሙ ሌሎች ጥቃቶች ከ 10 በላይ ተጨማሪ ሰዎች እንደተገደሉ ተነግሯል።

አሊ ቤንጃሚን ኩሊባሊ የተባሉት ዐቃቢ ህግ በያቴንጋ ግዛት በኮምሲልጋ ፣ ኖዲን እና ሶሮይ መንደሮች ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት መረጃ እንደረሳቸው እና በጊዜያዊው ቆጠራ መሰረት ወደ 170 የሚጠጉ ሰዎች እንደተገደሉ መታወቁን ተናግረዋል ።

የሰሜናዊቷ ከተማ ኦዋሂጉያ አቃቤ ህግ በማንም ቡድን ላይ ጣታቸውን ሳይቀስሩ በሰጡት መግለጫ ፣ ጥቃት አድራሾቹ ተጨማሪ ሰዎችን እንዳቆሰሉ እና የንብረት ውድመት እንዳስከተሉ አክለው አስታውቀዋል።መሥሪያ ቤታቸው ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ መስጠቱን እንዲሁም መረጃ እንዲያቀብላቸው ለህዝብ ጥሪ መደረጉን ተናግረዋል።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት ከተጎጂዎቹ መካከል በርካታ ሴቶች እና ህጻናት ይገኙበታል።

የአካባቢው የጸጥታ ምንጮች ጥቃቶቹ በናቲያቦኒ ገጠራማ ማህበረሰብ ውስጥ በሚገኝ መስጊድ እና በኤስሳካኔ መንደር ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስትያን ውስጥ በተመሳሳይ ቀን ከተከሰቱት ነፍስ የቀጠፉ ጥቃቶች የተለዩ ናቸው ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ በእነዚያ ጥቃቶች የተደሉትን ሰዎች ቁጥር እስካሁን ይፋ አላደረጉም። ነገር ግን አንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኑ ሹም በጥቃቱ ቢያንስ 15 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን በወቅቱ ተናግረዋል።


ቡርኪናፋሶ ከ2015 የአውሮፓዊያኑ ዘመን ጀምሮ ከጎረቤት ሀገር ማሊ መነሻውን አድርጎ በተስፋፋው ፣ ከአልቃይዳ እና እስላማዊ መንግስት ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው አማፂያ ጥቃት ጋር ስትታገል ቆይታለች።

በአለመረጋጋት ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው ሳህል ቀጠና ደሃ ሀገራት አንዷ መሆኗ በሚነግርላት ቡርኪናፋሶ በሰነበተው ግጭት ወደ 20,000 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

መንግስት በሀገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት መግታት አለመቻሉ የፈጠረው ቁጣ በአውሮፓዊያኑ 2022 ለተፈጸሙ ሁለት መፈንቅለ መንግስቶች ሚና እንደነበረው ተወስቷል።

ሀገሪቱን በብርቱ ክንድ እየመሩ ያሉት ኢብራሂም ትራወሬ ከአማጺያን ጋር ለሚያደርጉት ፍልሚያ ቅድሚያ ሰጥተዋል ። ዘገባው የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG