በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓድዋ ድል በዓል ላይ ሊታደሙ ወጥተው የታሰሩ ጋዜጠኞች አመሻሽ ላይ ተለቀቁ


ፎቶ ፋይል- 126ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓለ በአዲስ አበባ ከተማ ሲከበር
ፎቶ ፋይል- 126ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓለ በአዲስ አበባ ከተማ ሲከበር

የአዲስ አበባው የዓድዋ በዓል አከባበር ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአከባበሩ እና ክብረበዓሉ ከሚካሔድበት ቦታ ጋራ በተገናኘ ከፍተኛ ውዝግቦች የታዩበት 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ዛሬ የካቲት 23 ቀን ከሦስት ሳምንታት በፊት በተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተከብሯል።

ወትሮውን በፒያሳ ዳግማዊ ዐፄ ሚኒልክ አደባባይ በዓሉን ያከብሩ የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ዛሬ በአደባባዩም ይሁን ከአደባባዩ ትይዩ በስተደቡብ ዝቅ ብሎ በታነፀው የድሉ መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ በዓሉን ማክበር የሚችሉበትን ዕድል አላገኙም።

በዙሪያው ከፍተኛ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች፣ አስቀድሞ መግቢያ ፈቃድ ከተሰጣቸው ውጭ ወደ ስፍራው ማንም ሰው እንዳይገባ ከማለዳው ጀምሮ ከፍተኛ ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበር በስፍራው የነበሩ የአሜሪካ ድምፅ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች መታዘብ ችለዋል። የፖሊሶች ጥበቃ እና ክትትል ከሰዓትም ቀጥሎ መዋሉን እና እስከ ቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ወደ ሚኒሊክ አደባባይ አቅጣጫ ማለፍ እንደማይቻልም ተመልክተዋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት አዘጋጅነት በተከበረው በ128ኛው የድሉ መታሰቢያ በዓል ላይ በመንግሥት የተጋበዙ ታዳሚያን ብቻ ተሳትፈዋል። በየዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት የሚዘከረው የዓድዋ ድል፣ መከበር የጀመረው ጦርነቱ ከተደረገበት 1888 ዓ.ም. ከሰባት ዓመት በኋላ ነው፡፡

በሌላ በኩል በዓሉ ላይ ለመሳተፍ የተዘጋጁ “የዓድዋ ባዶ እግር” ፕሮጀክት ተሳታፊ 25 ጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎችም ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በእስር ላይ ውለው ተለቀዋል።

ስለሁኔታው ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየቱን የሰጠ እና ስሙን እንዳንጠቅስ የጠየቀ አንድ የፕሮጄክቱ አባል፣ በፖሊስ የተያዙት “ዓድ ባዶ እግር” በሚል ስያሜ፣ የዓድዋ ዘማቾችን ለማስታወስ፣ ከስድስት ኪሎ አካባቢ በባዶ እግራቸው ወደ ፒያሳ ሚኒሊክ አደባባይ ለመጓዝ ቀድመው ወደ መነሻው ስፍራ የደረሱ 25 አባላት ታስረው መዋላቸውን እና አመሻሹ ላይ መለቀቃቸውን ገልፀውልናል።

የ”ባዶ እግር” ፕሮጄክት አባላት፣ ለላለፉት ሦስት ዓመታት መነሻቸውን አራት ኪሎ አካባቢ በማድረግ በዓሉን ወደ ሚያከብሩበት የሚኒሊክ አደባባይ በባዶ እግራቸው ሲጓዙ እንደነበር ያስታወሰው አስተያየት ሰጪው፣ ዘንድሮ መነሻቸውን ስድስት ኪሎ ለማድረግ ወስነው በስፍራው ከማለዳ ጀምሮ በመሰባሰብ ላይ እንደነበሩ ተናግሯል።

ቀድመው ደርሰው ሌሎችን በመጠባበቅ ላይ እያሉ ከተያዙት ጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች መካከል፣ የብሔራዊ ጣቢያው የኢቢሲ፣ የፋና እና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም በግል የሚሠሩ የሚዲያ ባለሞያዎች ይገኙበታል።

25ቱ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወደሚገኝ ላዛሪስ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ቃላቸውን መስጠታቸውን፣ አስተያየቱን የሰጠን የፕሮጀክቱ አባል ገልጿል።

ስሜን አትጥቀሱ ያለን አስተያየት ሰጪው፣ የ”ባዶ እግር” ፕሮጄክት መስራቹን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ብስራት መንግሥቱን ጨምሮ 25ቱ ግለሰቦች በፖሊስ ጣቢያው ከዋሉ በኋላ አመሻሽ ላይ ከ12 ሰዓት በኋላ በመታወቂያ ዋስ እንደተለቀቁ ገልጿል፡፡ የአሜሪካ ድምፅም ይህንኑ አረጋግጧል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ክብረ በዓል ላይ፣ በሚኒሊክ አደባባይ በዓሉ እንዳይከበር ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወስደውታል በተባለ እርምጃ አንድ ሰው ሲገደል፣ በፒያሳው የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ አባቶችን ጨምሮ በርካቶች መጎዳታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት በአዲስ አበባ በኹለት ገጽታዎች ተከበረ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:02 0:00

ዘንድሮ ደግሞ፣ በዓሉን እንደቀድሞው በሚኒሊክ አደባባይ ማክፈር የሚፈልጉ ዜጎች ወደ አካባቢውም መድረስ አልቻሉም፡፡ በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በነበረው ክብረ በዓል ላይም የመታደም ዕድል አላገኙም፡፡

የአሜሪካ ድምፅን ጨምሮ፣ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ያሉ የመገናኛ ብዙኃንም በዓድዋ ሙዚየም የነበረውን በዓል ለመዘገብ ፈቃድ አልተሰጣቸውም፡፡

መንግሥት በዓሉ ከወትሮው በተለየ ድምቀት መከበሩን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል፣ በዓሉን አዓደባባይ የሚያከብሩበት ዕድል ዝግ መሆኑ “ቅሬታ እንደፈጠረባቸው” አስተያየታቸውን የሰጡን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

በዓሉን በድምቀት ከሚያከብሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆነው አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን “ዛሬ በመከልከሌ በዓሌን ማክበር አልቻልኩም፤ ደስ የማይል ስሜት አለው” ብሏል።

“ዓድዋ ተራ የፖለቲካ ጨዋታ መሆን አይገባውም” ያለው አርቲስቱ፣ “በጊዜ የማይቀያየር የሰው ልጅ ታሪክ የሆነን ድል ወስደህ ለዘመን ፖለቲካ ስታውለው ጠረኑ ደስ አይልም” ሲል ከአከባበሩ ጋር በተገናኘ ያለውን ንትርክ ተቃውሟል፡፡

“የበዓሉን አከባበር መቀየር የተፈለገው አላስፈላጊ ክርክር እንድናደርግ ታስቦ ነው። ታሪኩን የማይመጥን ክርክር ደግሞ ተገቢ አይደለም” ሲልም ሁኔታው እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጭ ደግሞ፣ በአድዋ ድልድይ አካባቢም ከፍተኛ ጥበቃ ሲደረግ እንደነበረ ተናግሯል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ንግድ ቤቶቸም በፖሊስ ትዕዛዝ ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ገልጿል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የዓድዋ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በወቅቱ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ በነበሩ ገዢዎች ማንነት ላይ በኢትዮጵያውያን መካከል ግልፅ ልዩነት መንፀባረቅ ጀምሯል።

የአድዋ ድል በዓል ማክበሪያ ቦታ ውዝግብ እልባት አግኝቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:19 0:00

ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ የገለፁት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚታዩ ልዩነቶች መፍትሔ እንደሚያሻቸው አመልክተዋል።

በዛሬው እስርና በነዋሪዎቹ ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ለኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ያደረግነው የስልክ ሙከራ አልተሳካም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG