በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው ኬንያዊው የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኬልቪን ኪፕቱም


በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው ኬንያዊው የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኬልቪን ኪፕቱም
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:04 0:00

በረጅም ርቀት ኮከብ ሯጭ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት የዓለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬልቪን ኪፕቱም፣ ከአሠልጣኙ ጋራ በደረሰበት የመኪና አደጋ ትላንት እሁድ የካቲት 3/2016 ዓ.ም ህይወቱ አልፏል።

ባለፈው ዓመት ቺካጎ ላይ በተካሄደው ውድድር የዓለም ክብረወሰን የሰበረው የ24 ዓመቱ ኪፕቱም በማራቶን ፣ ከረጅም ዓመታት በኋላ በረጅም ርቀት ሩጫ አስደናቂ ውጤት ያመጣሉ ተብለው ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች አንዱ ነው። በነሐሴ ወር በፓሪስ በሚካሄደው ማራቶን ወርቅ ያመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተፎካካሪዎችም አንዱ ነበር።

ኬንያዊው ኪፕቱም እና ሩዋንዳዊው አሠልጣኙ ጌርቪስ ኻኪዚማና በመኪና አደጋው ህይወታቸው ያለፈው ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ መሆኑን፣ ኬንያዊቷ አትሌት ሚልካ ቼሞስ ለአሶስዬትድ ፕሬስ ገልጻለች።

ቼሞስ ከአደጋው በኋላ የተወሰዱበት ሆስፒታል የነበረች ሲሆን፣ አስክሬናቸውን ማየቷንም ተናግራለች።

ቼሞስ ከሚተናነቃት እምባ ጋር እየታገለች "ኬልቪንን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ መግለፅ አልችልም" ብላለች።

የመኪና አደጋው የደረሰው በምዕራብ ኬንያ፣ ኤልዶሬት እና ካፕታጋት ከተሞች መካከል ላይ ባለው መንገድ ላይ መሆኑን ያስረዳችው ቼሞስ ስፍራው ከባህር ወለል ባለው ከፍታ እና ለኬንያውያን እና ከመላው ዓለም ለሚመጡ የረጅም ርቀት ሯጮች ለሥልጠና የተመቸ መሆኑን ገልጻለች። ኪፕቱም ተወልዶ ያደገው በዚሁ አካባቢ ነው።

ቼሞስ የአትሌቱን የሕልፈት ዜና ከሰማች በኃላ ከሌሎች አትሌቶች እና የኪፕቱም ቤተሰቦች ጋር ወደ ሆስፒታል መሄዷን ገልፃ፣ የኪፕቱምን አባት ጨምሮ ቤተሰቦቹ አስክሬኑን አይተው ማንነቱን ማረጋገጣቸውንም ተናግራለች።

የካፕታጋት ከተማ የፖሊስ ኃላፊ ዴኒስ ሙጋ፣ መኪናውን ያሽከረክር የነበረው እራሱ ኪፕቱም መሆኑን እና ሌላ አደጋ የደረሰበት መኪና አለመኖሩን ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG