በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ትናንት ዓርብ በድንገት አውራ ጎዳና ላይ ሊያርፍ ስለተገደደው የግል አውሮፕላን ጉዳይ የፌዴራል ባለሥልጣኖች ምርመራ መጀመራቸው ታውቋል።
አውሮፕላኑ አውራ ጎዳና ላይ ሲያርፍ ከአንድ መኪና ጋራ ሲጋጭ፣ መኪናው በተራው ሌሎችን ሲገጭ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አውሮፕላኑ ትናንት ዓርብ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ከሩብ አካባቢ መንገድ ላይ ለማረፍ ሲገደድ፣ በውስጡ አምስት ሰዎችን ይዞ እንደነበር የፌዴራሉ አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታውቋል።
የአካባቢው ፖሊስ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ሲያረጋግጥ፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ ይጓዙ የነበሩት፣ ወይስ ግጭት የደረሰባቸው መኪኖች ውስጥ የነበሩት ይሁኑ ግልጽ አላደረገም።
ብሪያና ዎከር የተባለች አሽከርካሪ፣ የአውሮፕላኑ ክንፍ ከፊቷ የነበረውን መኪና ጎትቶ ከግድግዳ እንዳጋጨው መመልከቷን ለአሶስዬትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ተናግራለች፡፡
ዎከር እና ጓደኛዋ አውሮፕላኑ ወደ መሬት በመውረድ ላይ ሳለ በመመልከታቸው፣ መኪናቸውን አብርደው ለጥቂት መትረፋቸውን ተናግረዋል።
አብራሪው በአካባቢው በነበረው አየር ማረፊያ እንዲያርፍ ፈቃድ ያገኘ ቢሆንም፣ ሁለቱም ሞተሮች በመበላሸታቸው ማረፊያው ቦታ መድረስ እንደማይችል እና ወዲያውኑ ባገኘው ቦታ ማረፍ እንደሚገደድ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም