በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ክልል አለመረጋጋት ኤችአይቪ/ኤድስን እያገዘ ነው


በአማራ ክልል አለመረጋጋት ኤችአይቪ/ኤድስን እያገዘ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:11 0:00

አማራ ክልል ውስጥ በቀጠለው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከአምስት ሺህ የሚበልጡ የኤችአይቪ/ኤድስ ህክምና ተከታታዮች ለማቋረጥ መገደዳቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶችን በተፈለገው መጠን ለማንቀሳቀስ አለመቻሉን የፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙሉነሽ ተስፋ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስቴር ደግሞ ኤችአይቪ በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑ በተዘገበበት አማራ ክልል የአየር ትራንስፖርትን እንደ አማራጭ በመጠቀም ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

በተለይ በክልሉ ምዕራባዊ ዞኖች ተደጋግሞ የሚከሠተው የፀጥታ ችግር ህክምና እየተከታተሉ ባሉ ሰዎች ላይ ተደራራቢ አሉታዊ ጫናዎችን ማስከተሉን የአማራ ክልል ኤችአይቪ ፖዚቲቭ በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረት ለጤናና ልማት የሚባል ድርጅት አመልክቷል።

የአፈፃፀም ክፍተቶች ከግለሰቦች ጤና በተጨማሪ በሃገርአቀፍ ደረጃ የታቀዱ ሥራዎችን ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ሲስተር ሙሉነሽ ተናግረዋል።

ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሁሉ የመድኃኒት አቅርቦትና ሕክምና እንዳይስተጓጎሉ፣ የጤና ባለሞያዎች ያለፍርሃት መንቀሳቀስ እንዲችሉና ሰብአዊ ድጋፎች በወቅቱ እንዲደርሱ ለማስቻል እንዲተባበሩ በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፈቃዱ ያደታ ጠይቀዋል።

603 ሺህ የሚሆን ሰው ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝና 507 ሺህ ሰው ህክምና እየተከታተለ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ ሕክምናና ክብካቤ ዴስክ ለቪኦኤ ገልጿል።

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ጨምሮ ግጭቶች ኤችአይቪ በመከላከልና በመቆጣጠር ሥራዎች ላይ ብርቱ ጫና ማሳደራቸውን በዚህ ምክንያትም በዓመት 11 ሺህ ሰው እንደሚሞት፣ ከስምንት ሺህ በላይ ሰው ለኤችአይቪ እንደሚጋልጥ ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG