በደቡብ ሶማሊያ በምትገኘው በለደ ሃዎ ከተማ በነውጠኞች ሳይፈጸም አልቀረም በተባለ ጥቃት ስድስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ትናንት ምሽት ደረሰ በተባለው ጥቃት፣ አንዲት ሶማሊያዊ ሴት መገደላቸውንም የቪኦኤ ሶማሊኛ ክፍል ያደረሰን ዘገባ አመልክቷል።
ነውጠኞች አንድ ግቢ ላይ አደረሱት በተባለው በዚህ ጥቃት አምስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ስድስቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የከተማው ባለሥልጣን አብድራሽድ አሮግ ለቪኦኤ የሶማሊኛ ክፍል ተናግረዋል።
ሌሎች ስድስት ኢትዮጵያውያንም ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለሥልጣኑ ጨምረው ገልፀዋል። ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የደረሰው ጥቃት፣ በከባድ መሣሪያ የታገዘ እንደነበር እና የተፈጸመውም የፀጥታ ኃይሎች ተራ በመቀያየር ላይ እንደነበሩ እንዲሁም ጥቃት አድራሹቹ ያንን አጋጣሚ መጠቀማቸውን ባለሥልጣኑ አስታውቀዋል።
ወታደሮች ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም፣ በደረሱ ጊዜ ግን ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ በርካቶች ሙትና ቁስለኛ ሆነው እንዳገኟቸው አሮግ ተናግረዋል።
የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ሁለት ወንዶች እና አራት ሴቶች መሆናቸው ሲታወቅ፣ በከተማው በንግድ እና በቤት ውስጥ ሠራተኝነት የተሠማሩ እንደነበርም ተመልክቷል።
በድንበር ላይ የምትገኘው በለደ ሃዎ ከተማ ከኬንያና ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንደሚያዘወትሯት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በጁባላንድ ግዛት የፀጥታ ሚኒስትር የሆኑት ዩሱፍ ዱማል ጥቃቱ በአል ሻባብ ተፈጽሟል ብለው እንደንደሚያምኑ ለቪኦኤ ሶማሊኛ አገልግሎት ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተሳተፉት አራት ታጣቂዎች እንደንበሩና የፀጥታ ኃይሎች ሲከተሏቸው በሞተር ብስክሌት እንዳመለጡ ባለሥልጣኑ ጨምረው ተናግረዋል።
የጥቃት ፈጻሚዎቹ ዓላማ ምን እንደሆን የተጠየቁት የፀጥታ ሚኒስትሩ፣ “በሶማሌዎች እና በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት መፍጠር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የጥቃት ሰለባዎቹ ዛሬ በበለድ ሃዎ ከተማ መቀበራቸው ታውቋል።