በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ጥር ውስጥ አራት የዕርዳታ ሠራተኞች ተገደሉ


በኢትዮጵያ ጥር ውስጥ አራት የዕርዳታ ሠራተኞች ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:42 0:00

በአማራ፣ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተራድዖ ሠራተኞች በፀጥታ መታወክ ምክንያት ለአደጋ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (በምኅፃር - ዩኤንኦቻ) ትላንት፤ ኀሙስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

በአንድ ወር ውስጥ አራት የሰብዓዊ አገልግሎት ሠራተኞች መገደላቸውንና ሁለቱ የተገደሉት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ከሣምንት በፊት መሆኑን፣ በጋምቤላ ክልል አንድ ሠራተኛ ባለፈው ወር (ታኅሣስ) መጨረሻ፣ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ደግሞ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ከሁለት ሣምንታት በፊት መገደላቸውን የማስተባበሪያ ቢሮው ለአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ በኢሜይል በሰጠው ምላሽ ገልጿል።

ግድያዎቹ የተፈፀሙት “ሠራተኞቹ በሥራቸው ምክንያት ዒላማ ተደርገው እንዳልሆነ ሪፖርቶቻችን ያሳያሉ” ብሏል ኦቻ። በአንፃሩ ግን ግድያዎቹ የሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን እንደሚያሳዩ ጠቁሟል።

“በአማራ ክልል የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ የወንጀል አድራጎቶችና የእርዳታ አቅርቦቶች ዝርፊያ ጨምረዋል” የሚለው የማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት ኦሮሚያ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት የእርዳታ ሠራተኞችን ለአጭር ጊዜ ማሰርና የማገት አድራጎቶች መባባሳቸውንም ጠቁሟል።

ጦርነት በተካሄደባቸው ትግራይና አፋር ክልሎች ውስጥ ያለው ሥጋት ደግሞ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየከፋ መጥቷል” የወንጀል አድራጎት መሆኑን ኦቻ በሪፖርቱ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ 46 የእርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውን የተናገረው የኦቻ ሪፖርት ሰላሣ ስድሥቱ የተገደሉት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት እንደነበር ገልጿል።

በሃገሪቱም በዓለምአቀፍም ሕግጋት መሠረት የእርዳታ ሠራተኞች በሁሉምና በምንም ዓይነት ጊዜያት ደኅንነታቸው ከጥቃትና ከጉዳት ሊጠበቅ እንደሚገባ ኦቻ አሳስቧል።

“በአማራ ክልል በመንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት ሲቪሎች ጭምር ዒላማ እየተደረጉና እየተገደሉ ናቸው” ሲል የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቶቹ ሲጎተጉት ይስተዋላል። “ሰላማዊ ሰዎችና ንብረቶቻቸው፣ እንዲሁም የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችና የአገልግሎት ተቋማት ዒላማ እንዳይደረጉ” ኮሚሽኑ ባለፈው ኅዳር ባወጣው መግለጫ በብርቱ አሳስቧል።

ግጭቶች ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉ ስለ ሲቪሎችና ስለ እርዳታ ሠራተኞች ደኅንነት እንዲያስቡ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ጠይቀዋል።

በእርዳታ ሠራተኞች ላይ ተፈፀሙ የተባሉ ግድያዎችንና የማሰርና የእገታ አድራጎቶችን አስመልክቶ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ አገልግሎቶች ማስተባበሪያ ቢሮ ላወጣው ሪፖርት ይህ ዘገባ እስከተጠቀረ ድረስ የክልሎቹ ባለሥልጣናት የሰጡት ምላሽ የለም።

XS
SM
MD
LG