በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ሉአላዊ ም/ቤት የኢጋድን የድርድር ጉባኤ ጥሪ እንደማይቀበል አስታወቀ


የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሞሃመድ አምዳን ዳጋሎ (ፎቶ ፋይል፣ ኤፒ)
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሞሃመድ አምዳን ዳጋሎ (ፎቶ ፋይል፣ ኤፒ)

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሱዳንን ግጭት በተመለከተ በሚቀጥለው ሳምንት በኡጋንዳ ለማካሄድ ባቀደው ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፍ በሱዳን ሠራዊት አዛዥ የሚመራው የአገሪቱ የሽግግር ሉአላዊ ም/ቤት አስታውቋል።

ም/ቤቱ በተጨማሪም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባላንጣ ከሆነው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሞሃመድ አምዳን ደጋሎ ጋር ግንኙነት መፍጠሩን አውግዟል።

ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው ግጭት፣ በአል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ሠራዊት ግዛቶችን እየተነጠቀ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሞሃመድ አምዳን ደጋሎ፣ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ መዲናዎችን ሲጎበኙ ሰንብተዋል።

በኢጋድ አማካይነት በኡጋንዳ በመጪው ሳምንት ሊካሄድ እቅድ በተያዘለት ጉቤኤ ላይ እንደማይገኝ ያስታወቀው ሉአላዊ ም/ቤቱ፣ “በሱዳን የተከሰቱት ሁኔታዎች የሱዳን የውስጥ ጉዳይ ናቸው” በማለት አስታውቋል።

ከስድስት የአፍሪካ አገራት ጉዞ የተመለሱት ዳጋሎ፣ በኢጋድ የቀረበውን የጉባኤ ጥሪ እንደተቀበሉት በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ አስታውቀዋል።

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ዳጋሎ መጋበዛቸው ሕግን የጣሰ እና ኢጋድ እንደ ተቋም ያለውን ተአማኒነት የሚጉዳ መሆኑን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ “አሸባሪ ሚሊሺያ” ሲል በጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተፈጸሙትን ሰቆቃዎች በተመለከተ ኢጋድ ዝምታን መርጧል ሲል ከሶ፣ የአባላት አገራት መሪዎች ብቻ መገኘት በሚገባቸው ጉባኤ ላይ ኃይሉን በመጋበዝ ሕጋዊ እውቅና ሰጥቷል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

የሱዳን ሠራዊት፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚያደርገውን ግስጋሴ መግታት ባለመቻሉ፣ አል ቡርሃን በዲፕሎማሲው መስክ መገለል እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG