በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የመንግሥት ሠራተኞች ፈተና እና ዳግመ ምደባ ጉዳይ አሳስቦናል” ፖለቲካ ፓርቲዎች


“የመንግሥት ሠራተኞች ፈተና እና ዳግመ ምደባ ጉዳይ አሳስቦናል” ፖለቲካ ፓርቲዎች
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:02 0:00

ሁለት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የመንግሥት ሠራተኞች ፈተና እና የዳግመ ምደባ ሒደት እንዳሳሰባቸው ገለፁ፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ፣ ባወጣው መግለጫ፣ አስተዳደሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ እናት ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ፈተና በመቃወም፣ ዳግመ ምደባውን ጨምሮ እንቅስቃሴው እንዲቆም ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ዙርያ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያ ደግሞ፣ “የሠራተኞች ፈተናም ይሁን ዳግመ ምደባ የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ህጎች መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ ለመንግሥት ሠራተኞች ተሰጠ ስለተባለው ፈተና እና እሱን ተከትሎ ስለሚደረገው የሠራተኞች ድልድል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ በማኅበራዊ ሚድያው እንዳብራራው፣ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎቶች መስጠት እንዲችሉ ልዩ ልዩ የማሻሻያ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ያብራራል፡፡ ከሥራዎቹ አንዱም፣ ሲቪል ሰርቪሱን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ማሟላት እንደሆነ የገለፀው ቢሮው፣ በዚህ መሠረት፣ ታህሳስ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከ 15 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ምዘና ፈተና መውሰዳቸውን አውስቷል፡፡ ይህንን እንቅስቃሴ በማስመልከት መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ፣ የሠራተኞቹን ፈተና እና ሊደረግ የታሰበውን ምደባ ተቃውሟል፡፡ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ብርሀኑ ስለ መግለጫው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ ፓርቲያቸው እንቅስቃሴውን በሁለት ምክንያቶች እንደሚቃወመው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፣ “የብቃት መመዘኛ” ያለውን ፈተና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መሰጠቱን አብራርቷል፡፡ በፈተናው ውጤት መሰረትም የሠራተኞች ምደባ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ - ኢዜማ፣ ጉዳዩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ በሒደቱ ሥጋት እንዳደረበት አስታውቋል፡፡ ስለ መግለጫው ለአሜሪካ ድምፅ ያብራሩት የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፣ በሠራተኞች ምደባው ሒደት የብሔር መስፈርት ሊካተት ነው መባሉ ፓርቲያቸውን እንዳሳሰበው ተናግረዋል፡፡

ስለ ብቃት መመዘኛ ፈተናው እና ሊደረግ ስለታሰበው ምደባ በተመለከተ፣ ከከተማው አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በጉዳዩ ዙርያ የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች፣ በመንግሥታዊው የብዙኃን መገናኛ፣ አዲስ ሚድያ ኔትዎርክ ላይ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ውይይት ግን፣ በአመራርነት ቦታ ላይ የሚመደቡ የአንድ ብሔር አባላት ብዛት ከ40 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለው ውሳኔ፣ የሁሉንም ብሔሮች ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይኸው መስፈርት፣ ዳይሬክተሮችን እና ቡድን መሪዎችን ብቻ እንጂ፣ የታችኛውን የሠራተኛ መደብ እንደማይመለከትም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የህዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር መምህር ዶ/ር ደፈረው ከበደ፣ ለመንግሥት ሠራተኞች የአቅም ምዘና ፈተና ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመው፣ ይህ ግን በሀገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ አማካኝነት ሊከናወን ይገባዋል ይላሉ፡፡

በቴሌቪዥን ውይይቱ ላይ የተሳተፉት የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች፣ ሊደረግ በታሰበው የሠራተኞች ምደባ፣ የሠራተኛው የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ አፈፃፀም እና የሥነምግባር ሁኔታ፣ የመስፈርቱ አካል እንደሆኑ ጠቀሰው፣ ፈተናው ከ 30-35 ከመቶ ብቻ እንደሚይዝ ገልፀዋል፡፡ ፈተናውን ያላለፉ ሰራተኞች፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመውሰድ፣ በሚመጥናቸው ቦታ ላይ እንደሚመደቡም ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG