በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በረሃብ “138 ሰው ሞቷል” - አፅቢ ወረዳ


በረሃብ “138 ሰው ሞቷል” - አፅቢ ወረዳ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:12 0:00

“በረሃብ ምክንያት የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው” ሲል በትግራይ ክልል የአፅቢ ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል።

"አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ" በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ 282 ሚልዮን ብር አሰባስቦ 64 ሺሕ ኵንታል እህል በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎች ማድረስ መጀመሩን ገልጿል።

የአፅቢ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መዝገበ ግርማይ በወረዳው በረሃብ ምክንያት 138 ሰው መሞቱን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።

በወረዳው ደራ የሚባል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃን ክፍለ የዘንድሮን የመሰለ ድርቅ አይተው እንደማያውቁ ጠቁመው አምስት ልጆች ይዘው ለረኃብ መጋለጣቸውን ገልፀዋል።

“ብዙ አረጋዊያን እናቶች ቤታቸውን ዘግተው ተኝተዋል። ከባድ ረሃብ ስላለ ወጣቱም አካባቢውን ጥሎ እየተሰደደ ነው። ወላጆቻችን፣ እህት ወንድሞቻችን እያየን ከሚሞቱብን በማለት ወደ አረብ አገሮች እየተሰደዱ ነው። ለመኖ የሚሆን ነገርም ባለመኖሩ እንስሣት እየሞቱ ነው" ብለው ሦስት ልጆቻቸው በረሃቡ ምክንያት ትምህርት እንዳቋረጡም አቶ ብርሃን ገልፀዋል።

ከወረዳው 33 ትምህርት ቤቶች ስምንቱ በረሃቡ ምክንያት ትምህርት ለማቆም መቃረባቸውን አስተዳደሪው አቶ መዝገበ ግርማይ አመልክተዋል።

“ጠፍተው ነበር” ያሏቸው እንደ ጆሮ ደግፍ፣ እከክ፣ የዐይን መታወክ፣ ተቅማጥ ያሉ የጤና ችግሮች በስፋት እየታዩ መሆናቸውንም አስተዳዳሪው ገልፀዋል። ከ5070 እናቶች 4078 በምግብ እጥረት የተጎዱ መሆኑን በጤና ባለሞያዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የፌደራሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም በአሁኑ ጊዜ በረሃብ ምክንያት ህይወት ማለፉን አላረጋገጥንም ብለው ነበር።

በትግራይ ክልል "አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ" በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ በበኩሉ በዚህ ዓመት በክልሉ ለተፈጠረው ድርቅ እና ረሃብ 10 ሚልዮን ኩንታል ምግብ እንደሚያስፈል አስታውቋል።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋይ ገብረእግዚአብሔር እህል በድርቅ ወደ ተጎዱ ወረዳዎች ከከትናንት በስተያ ቅዳሜ፣ ታህሳስ 27 / 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ማድረስ መጀመሩን ተናግረዋል።

“በዚህ ድርቅ ምክንያት በሰላሣ ስድስት ወረዳዎች 215 ቀበሌዎች ውስጥ 4 ሚልዮን ተኩል ሰው አስቸኳይ እርዳታ ይጠብቃል። ይህ መንግሥትና ለጋሾች ያካሄዱት ጥናት ነው። እነዚህን ምግብ በአስቸኳይ የሚያስፈልጋቸውን ለማገዝም በዚህ አንድ ዓመት አሥር ሚልዮን ኵንታል ወይም 40 ቢልዮን ብር ያስፈልጋል። አሁን በአንደኛው ዙር 32 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 425 ሺሕ ተጠቃሚዎች የሚታደል 64 ሺሕ ኩንታል እህል መላክ ጀምረናል” ብለዋል።

ይህ ከግለሰቦችና ከተቋማት በማሰባሰብ በቆሎ በመግዛት ወደ ተጎዱ አካባቢዎች መላክ የተጀመረው እህል ወደ ህዝቡ በቀጥታ እንዲደርስም ክትትል ይደረጋል ተብሏል።

በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅ “ለፖለቲካ ዓላማ እየዋለ ነው” ሲሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ወቅሰው ድርቁ “የ77ቱን ዓይነት አደጋ ደቅኗል መባሉ ፍፁም የተሳሳተ ነው” ብለው ነበር።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በሰጡት ምላሽ “ለረኃብ የተጋለጡ ሚልዮኖችን ለመታደግ የቀረበው ጥሪ ፖለቲካዊ መባል የለበትም ማለታቸው” አይዘነጋም።

XS
SM
MD
LG