የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ እ.ኤ.አ. በ 2020 የተሸነፉበትን ምርጫ ለመቀልበስ አድርገዋል በተባለው ጥረት የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ እኤአ በ2024 ከሚደረገው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር ስለመታገድ አለመታገዳቸው ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ትናንት ዓርብ አስታውቋል፡፡
መራጮች በቅርቡ በመላ አገሪቱ በሚደረጉ የፕሬዚዳንታዊ ቅድመ ምርጫዎች ድምጽ መስጠት ስለሚጀምሩ በፍጥነት ውሳኔ ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ዳኞች ማመናቸውን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ትረምፕ እኤአ ጥር 6፣ 2021 በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ (ካፒቶል) ላይ በተፈፀመው ጥቃት በነበራቸው ሚና የተነሳ በቅድመ ምርጫው ውድድር መሳተፍ አይችሉም ሲል የኮሎራዶ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት 4ለ3 በሆነ ድምጽ የወሰነው ባለፈው ወር ነበር፡፡
ትረምፕ ይህን ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የትረምፕን ይግባኝ ተገቢነት ተቀብሎ ጉዳዩን በመጭው የካቲት የሚመለከተው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለኮሎራዶው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ መሠረት የሆነውንና በ14ኛው የህገ መንግሥት ማሻሻያ “በአመፅ የተሳተፉ” ሰዎችን የመንግስት ሥልጣን እንዳይዙ የሚከለክለውን ድንጋጌ ትርጉም እና መነሻን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚመረምር ተመልክቷል፡፡
ትረምፕ በሜይን ክፍለ ግዛት በዲሞክራቱ የምርጫ ኃላፊ ሼና ቤሎውስ የተላለፈባቸውን ተመሳሳይ ውሳኔ ለዚያው ክፍለ ግዛት በተጠናል ይግባኝ ጠይቀዋል፡፡
ሁለቱም የኮሎራዶ እና የሜይን ውሳኔዎች ይግባኙ በውሳኔ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉበት እንደሚቆዩ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም