በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በግዛቷ ያሉ የውጭ ዜጎች የሰነዶቻቸውን ህጋዊነት እንዲያረጋግጡ አሳሰበች


ኢትዮጵያ በግዛቷ ያሉ የውጭ ዜጎች የሰነዶቻቸውን ህጋዊነት እንዲያረጋግጡ አሳሰበች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:44 0:00

በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሰነዶቻቸውን ህጋዊነት እንዲያረጋግጡ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በህገወጥ ሰነድ የሚኖሩ ከ20 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በሀሰተኛ ሰነድ እና ጊዜው ባለፈበት ሰነድ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ህገ ወጥነት እንደሆነ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የውጭ ዜጎች ይሄንን ተገንዝበው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ተቋሙ በመሔድ የሰነዶቻቸውን ህጋዊነት እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል፡፡

በተቀመጠው ቀነ-ገደብ በማይጠቀሙት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ ውሳኔው “ከለላ ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን አያካትትም” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች የመኖሪያ ሰነድን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፣ ህጋዊ ሰነድ ከመያዝ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውንና ህገወጥ ድርጊቶች መበራከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የመኖርያ ፈቃድ የሚያሰጡ የተለያዩ ቪዛዎች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመው፣ ሆኖም በርካቶች በሀሰተኛ ሰነዶችን እየኖሩ እንደሆነ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ስራዎች ስም ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስም ወንጅለዋል።

እርምጃው የውጭ ዜጎችን ከሀገር ማባረርን ያካትት እንደሆነ ግን አልጠቀሱም፡፡

በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ስደተኞች፣ ህጋዊ ሰነድ የመስጠት ሒደትና የከለላ ጠያቂዎች የምዝገባ አገልግሎት ከሦሰት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ መቋረጡን፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በዚህ ምክንያት፣ ስደተኞችና ከለላ ጠያቂዎች ህጋዊ ሰነድ የላችሁም በሚል ለእስር እየተዳረጉ መሆናቸውን እና ተገደው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረጉ እንደሆኑ ተቋማቱ በቅርቡ ባወጧቸው መግለጫዎች እና በሰጧቸው አስተያየቶች አንስተዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG