በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በስፋት ቀጥላለች


ጋዛ 2016
ጋዛ 2016

የእስራኤል ጦር ደቡባዊውን የጋዛ ከተማ ካን ዮኒስን በሌሊት የአየር ቦምብ እና የታንክ ድብደባ ማውደሙን ቀጥሏል። ጠንከር ያለው ዘመቻው እየተፈጸመ ያለው፤ ወደ ከተማይቱ ለመግባት ከሚጠበቀው የእስራኤል እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ እንደሆነ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አውታር ከጋዜጠኞቹ አንዱ በካን ዩኒስ እና ራፋህ ላይ ተከታታይ የመሳሪያ ድበደባዎች መፈጸማቸውን መዘገቡን አስታውቋል።

በግብፅ አቅራቢያ የምትገኘው ራፋህ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከጦርነቱ የተጠለሉባት ስፍራም ናት። በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጋዛ እስራኤል የኑሴይራት ካምፕ ላይ የአየር ድብደባ የፈጸመች ሲሆን የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ ውስጥ በቤቴ ላሂያ ሁለት የሃማስ መጠለያዎችን ደምስሻለሁ ሲል አስታውቋል።

በጋዛ ላይ የተፈጸሙት በርካታ የጥቃቶች ሪፖርቶች የወጡት የጋዛ የጤና ባለስልጣናት በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት በቅርቡ በጋዛ የተፈጸመው እና በእርዳታ መኪኖች ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉትን የእስራኤልን ጥቃት ተቃውመዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የተራድኦ አገልግሎት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ዳይሬክተር በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው ላይ አርብ ዕለት "የእስራኤል ወታደሮች በሰሜን ጋዛ በእስራኤል ጦር በተፈቀደ መንገድ ሲጓዙ በነበሩ የእርዳታ መኪኖች ላይ ተኩሰዋል" ብለዋል።

በተመሳሳይ የተ.መ.ድ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ዋና ጸሃፊ ማርቲን ግሪፊዝ ጥቃቱ “ሆነ ተብሎ በዒላማ የተደረገ” ነው ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ግጭቱ መቆም አለበት በረዲዔት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ህገወጥ” ነው ሲሉ አሳስበዋል።

በጥቃቱ አንድ መኪና የተጎዳ ሲሆን በሰው ላይ የደረሰ አደጋ እንደሌለ ተጠቁማል። እስካሁን ድረስ የእስራኤል ጦር ሰራዊትም ምላሹን አልሰጠም።

በሌላ በኩል የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት ፈንድ ዩኒሴፍ 600,000 ክትባቶችን በትላንትናው ዕለት ጋዛ አድርሻለሁ ሲል አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG