በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መብቶችን በብርቱ የጣሱ ሊከሰሱ ይገባል - የሽግግር ፍትኅ ቡድን


መብቶችን በብርቱ የጣሱ ሊከሰሱ ይገባል - የሽግግር ፍትኅ ቡድን
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:50 0:00

በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተሣተፉ ሊከሰሱ እንደሚገባ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች ቡድን ምክረሃሳብ አቅርቧል።

ክሱ መታየት ያለበት አዲስ በሚቋቋም ልዩ ፍርድ ቤት ቡድኑ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ሊተገበር ለታቀደው የሽግግር ፍትኅ እስከ ፖሊሲ ዝግጅት ያሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ተሰጥቶት ኅዳር 2015 ዓ.ም. የተቋቋመው 13 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ዛሬ ሪፖርት አውጥቷል።

ቡድኑ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አከናንኳቸው ባላቸው 58 ህዝባዊና ሌሎች 22 መድረኮች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች ላይ አተኩሮ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያካተተ የግብዓት ማሰባሰቢያ ምክክር መደረጉን አብራርቷል።

በስምንት የፖሊሲ አማራጮች ላይ በተደረገው ምክክር አብዛኞቹ ተሳታፊዎች የደገፏቸውና አቋም የወሰዱባቸው ዋና ዋና ግኝቶችንና ምክረሃሳቦቹንም ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል የወንጀል ተጠያቂነት ጉዳይ እንደሚገኝበት አመልክቷል።

ጉልህ በሆኑ ጥሰቶች ላይ ያተኮረ የክሥ ሂደት ሊኖር እንደሚገባ ግብዓቶቹን መነሻ አድርጎ የገለፀው የባለሙያዎቹ ቡድን ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው በሚረጋገጥ ሰዎች ላይ ክሥ ሊመሥረት እንደሚገባ እንደሚያሳስብ የባለሙያዎች ቡድኑ አባል ቃል ኪዳን ደረጀ ተናግረዋል። ክሱ በአዲስ ዐቃቤ ሕግ ተቋም መመራትና አዲስ በሚቋቋም ልዩ ፍርድ ቤት መታየት እንዳለበትም መክረዋል።

ሌላው የሽግግር ፍትሕ አካል የሆነው እውነት የማፈላለግ እና እርቅ ተግባር፣ በሁሉም ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሊተገበር እንደሚገባም ሪፖርቱ አሳስቧል። ይህም የተፈፀሙ ወይም ተፈፅመዋል የሚባሉ የበደል ትርክቶችና መሰል ችግሮች ዕልባት ሊያገኙ በሚችሉበት መንገድ መከናወን እንዳለበት የምክክሩ ተሳታፊዎች ማንፀባረቃቸውን ጠቅሷል። እውነት የማፈላለግ እና የዕርቅ ተግባራትም አዲስ በሚቋቋም ገለልተኛና ተቀባይነት ያለው የሃቅ አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተገልጿል። ኮሚሽኑ ሲቋቋም የውጭ ባለሙያዎችን ማካተት እንደሚኖርበት ቃልኪዳን ደረጀ ተናግረዋል።

በሪፖርቱ የተመለከተው ሌላው የሽግግር ፍትሕ አምድ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምኅረት ሲሆን ይህም አዲስ በሚቋቋመው ሃቅ አፈላላጊ ኮሚሽን መመራት እንዳለበት ተመልክቷል። ከፍተኛ የወንጀል ተሣትፎ አላቸው የሚባሉ አካላት በዚህ መካተት እንደሌለባቸውም ወ/ሮ ቃልኪዳን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ለተጎጂዎች የሚደረግ ማካካሻን የሚመለከተው የሽግግር ፍትኅ ሂደትም በሃቅ አፈላላጊው ኮሚሽን እንዲመራ የምክክሩ ተሣታፊዎችን ሃሳብ መነሻ በማድረግ የባለሙያዎች ቡድኑ መክሯል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከየትኛው ጊዜ ይጀምር በሚል ከቀረቡ አምስት አማራጮች ውስጥ “ለክሥ ጉዳይ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ለእውነት ማፈላለግ፣ እርቅ ማስፈንና ማካካሻ ጉዳይ ግን መረጃና ማስረጃ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ” የሚለው አማራጭ ተቀባይነት ማግኘቱ ተብራርቷል።

ከህዝብ የተገኙ የተባሉ ግብዓቶችን መነሻ በማድረግ ሃገራዊ የሽግግር ፍትኅ ፖሊሲ የማዘጋጀት ሥራው በአራት ሣምንታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የባለሙያዎች ቡድኑ አባልና አስተባባሪ ዶ/ር ታደሰ ካሣ ተናግረዋል።

ለሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ዝግጅት ግብዓቶችን ሲያቀርቡ ከነበሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አንዱ “የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች” ዋና ሥራ አስኪያጅ አምኃ መኮንን፣ እስካሁን ያለውን ሂደት አድንቀው በወንጀል ተጠያቂነት ዙሪያ ፖሊሲው ሊኖረው ይገባል ባሉት ይዘት ላይ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ተቋማዊ ማሻሻያ ስለሚያስፈልጋቸው ተቋማትም የባለሙያዎች ቡድኑ በዛሬው ሪፖርቱ ላይ ምክረሃሳብ አቅርቧል።

በሽግግር ፍትኅ ሂደቱ ላይ የሚኖሩ የህግ ክፍተቶችን ለማጥበብ ከዓለምአቀፍ ሕግ አንፃር ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፍ ሊቀረፅ እንደሚገባም ሪፖርቱ አሳስቧል።

ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ እውነትን ለማውጣትና ለእርቅ የሚሠራ፣ እንዲሁም ተጎጂዎችን የሚክስ የሽግግር ፍትኅ ተግባራዊ እንዲደረግ የተለያዩ ሃገሮችና ተቋማት ጥሪ እያሰሙ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በውይይት በመፍታትና በመላ ሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን፣ ለሽግግር ፍትኅ አፈፃፀም ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ትናንት በጋራ ባወጡት ሪፖርት ጠይቀዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

XS
SM
MD
LG