-
ዜለነስኪ የአየር ኃይል ፓይለቶችን አመሰገኑ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በዩክሬን ካኸርሰን ክልል፣ ሶስት የሩሲያ ተዋጊ ጄቶችን በጥይት የገደሉትን የአየር ሃይል አብራሪዎች አመሰገኑ፡፡
ዜለነስኪ አብራሪዎችን ያመሰገኑት በየእለቱ በሚያሰሙት የትናንት ዓርብ ንግግራቸው ነው፡፡
አብራሪዎቹን ወታደሮች ባመሰገኑበት በዚሁ ንግግራቸው "ምናልባት እያንዳንዱ የሩሲያ አብራሪ፣ ለእያንዳንዱ የሩሲያ ገዳይ የምንሰጠውን ምላሻችንን በሚገባ ይገነዘባል” ያሉት ዜለነስኪ - “አንዳቸውም ሳይቀጡ አይቀሩም" ሲሉ አክለዋል፡፡
የሩስያ አብራሪዎች እና የአውሮፕላኑ አባላት እጣ ፈንታ ወዲያውኑ አልታወቀም።
በሌላ በኩልም የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ዓርብ ባወጣው እለታዊው መረጃ በአንዳንድ ግንባሮች “የዩክሬን እና የሩሲያ ወታደሮች ሌላ ዓይነት ጠላት ገጥሟቸዋል” ሲል የአይጥ መንጋ እያሰቸገራቸው መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ሞቃታማ በነበረው የመኸር ወቅት በጦርነቱ ሳቢያ ያልተሰበሰበ ከፍተኛ ምርት በማሳው ላይ በመቆየቱና በየሜዳው ከተጣለው ምግብ ጋር በርካታ መጠን ያላቸው አይጦች መበራከታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
አይጦቹ ልክ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት እንዳደረጉት በተሽከርካሪዎችና በወታደራዊ መሣሪያዎች ውስጥ ሊደበቁ፣ የመሣሪዎቹን መሰረታዊ አካላትና ኬብሎችንም በጥርሳቸው ሊበጣጥሱ ይችላሉ ብሏል፡፡
ይህ የወታደሮቹን ሞራል ይጎዳል ያለው የሚኒስቴሩ መረጃ፣ ምንም እንኳ ማረጋገጫ ባይገኝለትም፣ በሩሲያ ወታደሮች ላይ በአይጦቹ ሳቢያ ታይተዋል የተባሉ የበሽታ ዓይነቶች እየበዙ መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
መድረክ / ፎረም