በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በትግራይ እና በዐማራ ክልሎች ሥራ እንዳቆመ አስታወቀ


የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በትግራይ እና በዐማራ ክልሎች ሥራ እንዳቆመ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:51 0:00

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በዐማራ እና በትግራይ ክልሎች ሥራውን እያከናወነ እንዳልኾነ አስታወቀ።

ከሁለቱ ክልሎች ውጭ በሌሎች ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች፣ ተሳታፊዎችንና የምክክር አጀንዳ አቅራቢዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ፣ ኮሚሽኑ ዛሬ ዐርብ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ፣ በትግራይ እና በዐማራ ክልሎች ሥራውን ለመቀጠል ሊከተለው ስለሚችለው መንገድ፣ ከልዩ ልዩ አካላት ጋራ እየተመካከረ እንደሚገኝ፣ መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡

ይህም ኾኖ፣ በዐማራ እና በትግራይ ክልሎች፣ ተሳታፊዎችን ለመለየት ቅድመ ኹኔታዎች እንደተጠናቀቁ ያነሡት ቃል አቀባዩ፣ ወቅታዊ ኹኔታውን ከግምት በማስገባት መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል፣ ከጦርነት የመውጣት ሒደት ውስጥ ቢኾንም፣ ሌሎችም ውስብስብ ችግሮች እንዳሉና ኅብረተሰቡ በብዛት እና በንቃት የሚሳተፍበትን የተረጋጋ ዐውድ ለመፍጠር ጊዜ እንደሚፈልግ አቶ ጥበቡ አመልክተዋል፡፡ ምክክሩ አሳታፊ እና አካታች መኾን እንዳለበት ያስገነዘቡት ቃል አቀባዩ፣ ይህም በድርቅ እና በረኀብ እየተካለበ ባለበት ኹኔታ “እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፤ መመካከርን፣ መከባበርን፣ መደማመጥን፣ መቻቻልንና ትዕግሥትን ይጠይቃል፤ ስለዚኽ ሒደቶችን ተከትሎ፣ ከእውነታው ጋራ በሚቀራረብ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል፤” ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ከኹለቱ ክልሎች ውጭ ባሉት አካባቢዎች፣ በተለያየ መጠን፣ የወረዳ ተሳታፊዎችንና አጀንዳ አቅራቢ ተወካዮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ፣ 327 ወረዳዎች አጀንዳ የሚያቀርቡ ወኪሎቻቸውን ለይተው እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ጥበቡ፣ የልየታ ሥራውን ያጠናቀቁ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች አሉ፡፡ እስከ አኹን በደረሱበት ደረጃ፣ በሲዳማ በ45 ወረዳዎች፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 57 ወረዳዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 24 ወረዳዎች፣ በሐረሪ 9፣ በድሬዳዋ 12፣ በጋምቤላ 14፣ በዐዲስ አበባ 119 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተሳታፊዎችን ብቻ ሳይኾን፣ በአጀንዳዎች ላይ ሐሳብ የሚሰጡ ተወካዮች የተጠናቀቁባቸው እንደኾኑ ዘርዝረዋል፡፡

እስከ አኹን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል ወደ 327 ወረዳዎች፣ ሙሉ በሙሉ ተወካዮቻቸውን መርጠው እንደጨረሱም አክለዋል። በመላው ኢትዮጵያ፣ በተለያየ መጠን ሥራ እየተሠራባቸው ያሉ ወረዳዎች 700 እንደኾኑም፣ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ግጭት እየተካሔደበት የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል፣ ከ379 ወረዳዎች ውስጥ 45 በመቶ በሚኾኑት(171 ወረዳዎች) ውስጥ፣ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በማያግባቡ መሠረታዊ እንዲሁም የልዩነት እና የግጭት መንሥኤ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በሕዝቦች መካከል ምክክር ተደርጎ መግባባት እንዲፈጠር የማስቻል ተልእኮ አንግቦ እና በዐዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ፣ ሁለት ዓመቱን ሊደፍን ከሦስት ወራት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል፡፡ ኮሚሽኑ ለሦስት ዓመት የሥራ ጊዜ ቢቋቋምም፣ ግጭቶች በዕቅዱ መሠረት እንዳይጓዝ አድርገውታል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ፣ ከአንድ ወር በፊት፣ የመሥሪያ ቤታቸውን የአራት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በግጭቶች እና ሌሎች ወቅታዊ ችግሮች ምክንያት፣ ኮሚሽኑ ሥራውን በዕቅዱ መሠረት ማከናወን እንዳልቻለ አመልክተው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የትጥቅ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ፣ ምክር ቤቱ በመንግሥት የአስፈጻሚ አካል ላይ ጫና እንዲያደርግም ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡

ይኹን እንጂ፣ ከፕሪቶርያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት ለማቆም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል፣ በሁለት ዙሮች የተደረጉ ድርድሮች ያለስምምነት መጠናቀቃቸው ይታወቃል፡፡ በዐማራ ክልል የቀጠለው ግጭትም በድርድር እንዲፈታ ግፊቶች ቢቀጥሉም፣ እስከ አኹን በይፋ የተጀመረ ድርድርም ይኹን የድርድር እንቅስቃሴ የለም፡፡

XS
SM
MD
LG