በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ቀንድ ከዱባዩ የአየር ንብረት ጉባዔ ምን አገኘ?


የአፍሪካ ቀንድ ከዱባዩ የአየር ንብረት ጉባዔ ምን አገኘ?
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:21 0:00

ለሁለት ሳምንታት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሲካሄድ የነበረው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ፣ ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራት፣ ከከርሰ ምድር የሚወጣ ድፍድፍ ነዳጅን በሂደት ለመቀነስ በገቡት ስምምነት ተጠናቋል። ኾኖም ከከርሰ ምድር የሚወጣ ኃይልን በሂደት መጠቀም ወደማቆም መሸጋገርን ይጠብቁ የነበሩ የጉባዔው ተሳታፊ ሀገራት በስምምነቱ ደስተኛ አይደሉም።

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ፣ ዱባይ ላይ የተካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ (ክፕ 28) ከሁለት ሳምንት በፊት የጀመረው ትልልቅ ተስፋዎችን ሰንቆ ነበር። በተለይ ከከርሰ ምድር በሚወጣ ድፍድፍ ነዳጅ በገንዘብ ተጠቃሚ የሆኑት ያደጉ ሀገራት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉ ሀገራት እንዲያደርጉ የሚጠበቀው የገንዘብ ድጋፍ እና፣ የያዝነው ምዕተ አመት ከመጠናቀቁ በፊት የዓለም ሙቀት ከ1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች እንዲሆን እቅድ መንደርደሪያ የሚሆኑ ውሳኔዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠብቀው ነበር። በጉባዔው መክፈቻ ቀን ለኪሳራ እና ጉዳት እንዲቋቋም የተወሰነው ፈንድ ወደ ተግባር እንዲገባ መወሰኑም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአየር ንብረት ተፅእኖ የበረታ ክንዱን የሚያሳርፍባቸው ሀገራትን ያስደሰተ እንደነበር በወርልድ ሪሶርስ ተቋም ተንታኝ የሆኑት እና በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በድርድሮች ላይ የሚሳተፉት አቶ ያሬድ አበራ ይገልፃሉ።

ባለፉት 40 አመታት ባልታየ ድርቅ ሲሰቃይ የነበረው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አሁን የተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከ1.6 ሚሊየን በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 396 ሺህ የሚሆኑት የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አክሽን አጌንስት ሀንገር የተሰኘው በአፍሪካ ቀንድ ረሃብን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ርዳታ ሰጪ ተቋም አስታውቋል።

በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ጎርፍ መንገዶችን እና ቤቶችን ያጥለቀለቀ ሲሆን፣ የውሃ ምንጮች እንዲበቀሉ እና የጤና ተቋማት እንዲወድሙ በማድረጉ በክልሉ ለበሽታ ተጋላጭነት ጨምሯል።

በአየርን ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱት እነዚህ ተደራራቢ ጉዳቶችን እያስተናገደች ያለችው ኢትዮጵያ እና በቀንዱ የሚገኙት እንደ ኬንያ እና ሶማሊያ ያሉ ሀገራት፣ ከኪሳራ እና ጉዳት ፈንዱ እንዴት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ያሬድ ያስረዳሉ።

ይህ የገንዘብ ድጋፍ ዜና ለታዳጊ ሀገራት መልካም ዜና ይሁን እንጂ ተግባር ላይ ለመዋል ግን ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ይኖርበታል። አንደኛው ችግር የበለፀጉ ሀገራት ቃል የገቡትን ገንዘብ በወቅቱ የመስጠታቸው ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ የደን ልማት ሚኒስትር፣ የደን ስነ-ምህዳር ባለሙያ እና 'ሬድ ፕላስ' የተባለ የደን ልማት ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ይተብቱ ሞገስ እንደሚሉት የበለፀጉ ሀገራት ለፈንዱ ያዋጡት ገንዘብ በጉባዔው መጀመሪያ ላይ የታየውን ተስፋ እንዳቀዘቀዘው ይገልፃሉ።

ሌላው ችግር ታዳጊ ሀገራት በሚደርስባቸው ጉዳት ልክ ካሳ ለማግኘት፣ በጥናት የተደገፈ መረጃ ማቅረብ የሚኖርባቸው መሆኑ ነው። ዶክተር ይተብቱ ይህን የሚያደርጉ የባለሙያ ማዕከላት አለመኖራቸው የድጋፉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንደሚያደርጋቸው ኢትዮጵያን ምሳሌ አድርገው ያስረዳሉ።

እ.አ.አ በ2015 ፓሪስ ላይ በተካሄድው 21ኛው ጉባዔ የዓለም ሀገራት በፈረሙት የፓሪስ ስምምነት የዓለም ሙቀትን 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ለመገድብ ተስማምተው ነበር። ይህንንም ለማሳካት እ.አ.አ በ2030 ሙቀት ማመቅ የሚችሉ የጋዝ አይነቶችን በ43 ከመቶ ለመቀነስ እና በ2050 ዓለምን ከካርበንዳይኦክሳይድ የፀዳ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

በ28ኛው የአየር ንብረት ጉባዔ ትልቁን አጀንዳ የያዘውም፣ ዓለምን እየጎዳ ላለው ሙቀት ተጠያቂ የሆነውን ከከርሰ ምድር የሚወጣ ኃይልን መጠቀም እንዲቆም በሚፈልጉ እና በማይፈጉ ሀገራት መካከል የሚካሄደው ውይይት ነው።

ከጉባዔው መጀመር ቀደም ብሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ያደረገው ግሎባል ስቶክቴክ የተሰኘው ሪፖርት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሙቀትን ከ1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለመገደብ ከያዘው እቅድ በጣም የራቀ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን፣ በምትኩ የካርበንዳዮክሳይድ ልቀት መጨመሩን እና 80 ከመቶ የዓለም ኃይል አቅርቦት ከከሰል ድንጋይ፣ ዘይት እና ከተፈጥሮ ጋዞች የሚገኝ መሆኑን አብራርቷል።

የዘንድሮው የአየር ንብረቱ ጉባዔ ስምምነት ያሳካዋል ተብሎ የተጠበቀው፣እነዚህን የከርሰ ምድር ኃይሎች "በፍጥነት መጠቀም" ማቆም የሚያስችል የውሳኔ ሀሳብ አለመሳካቱ በርካታ ታዳጊ ሀገራትን፣ ትንንሽ ደሴቶችን እና የአየር ንብረት ተሟጋቾችን በእጅጉ አሳዝኗል። የውሳኔ ሀሳቡ 'ምክንያታዊ፣ ስርዓት ባለው እና ፍትሃዊ' በሆነ መልኩ መጠቀምን የሚያበረታታ መሆኑም፣ በርካታ ሀገራትን አስቆጥቷል። ለዚህ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ተፅእኖ ማድረጋቸውን ዶክተር ይተብቱ ያመለክታሉ።

እንደ ሳዑዲ አረብያ ያሉ ዋና የነዳጅ አምራች አገሮች የከርሰ ምድር ኃይልን ቀስ በቀስ መጠቀም ማቆም የሚለውን ቋንቋ የማይቀበሉ ሲሆን ለመጪዎቹ አመታት ድፍድፍ ነጃቸውን መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ። በዛው ልክ ጉዳቶችን እያደረሰ የሚገኘው አየር ንብረት ልውጥ ግን መፍትሄው ግልፅ ነው ይላሉ ዶክተር ይተብቱ።

በዓለም ላይ ትልቅ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት ያላቸው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ በዘንድሮው ጉባዔ ላይ አለመገኘታቸው በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ዋና የነዳጅ አምራች የሆነቸው አሜሪካ ለኪሳራ እና ጉዳት ፈንዱ 24.5 ሚሊየን ዶላር ብቻ ለመስጠት ቃል መግባቷም የቁርጠኝነት ጥያቄ ተነስቶባታል። ከአሜሪካ በተጨማሪ ለፈንዱ እስከ 700 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል የገቡ ሀገራት ቃላቸውን ይጠብቁ እንደሆነም ይታያል። እስከዛው በድርቅ እና በአስከፊ ድርቅ ለከፍተኛ ረሃብ እና መፈናቀል የተጋለጡት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች በተስፋ ይጠብቃሉ።

XS
SM
MD
LG