በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀሩ ፕሬዚዳንታዊ ቢኾን የተጠያቂነት ክፍተቶችን ለመቅረፍ ያግዛል ተባለ


በኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀሩ ፕሬዚዳንታዊ ቢኾን የተጠያቂነት ክፍተቶችን ለመቅረፍ ያግዛል ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:21 0:00

የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀር፣ ተጠያቂነትን በማዳከም ለወንጀል እና ለመብቶች ጥሰቶች ዕድል የሚሰጥ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት አስታወቀ።

ኅብረቱ፣ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ሊኾኑ ይገባል ያላቸውን አራት ቁልፍ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን እንደለየ ገልጿል፡፡

ከአጀንዳዎቹ ውስጥ፣ ለበርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በምክንያትነት የተጠቀሰው የተጠያቂነት ክፍተት እንደተካተተና ለዚኽም መንግሥታዊ አወቃቀሩ ዋና ምክንያት እንደኾነ፣ የኅብረቱ ዲሬክተር መስዑድ ገበየሁ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት፣ በጥናት እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋራ ባደረገው ውይይት እንደለያቸው የገለጻቸውን አራት ቁልፍ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቅርቧል፡፡

የሲቪክ ተቋማትንና ዲፕሎማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች በተገኙበት ይፋ ከተደረጉት የኅብረቱ የሀገራዊ ምክክር አራት ቁልፍ አጀንዳዎች መካከል፣ ተጠያቂነት እንደሚገኝበት፣ የኅብረቱ ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ ይናገራሉ።

በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል፣ ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት እና የጎንዮሽም ኾነ ቀጥተኛ ተጠያቂነት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት የኅብረቱ ዲሬክተር፣ “ማንም ሰው የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት ፈጽሞ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥርዓት ካልኖረ፣ ብንነጋገርም ብንስማማም ያለንበት አዙሪት ውስጥ መቆየታችን የማይቀር ነው፤” ይላሉ፡፡ በምክክሩ ሒደቱ ውስጥ፣ የተጠያቂነት ጉዳይ እንደ አንድ አጀንዳ እንዲታይ የተለየውም በዚኽ ምክንያት እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡

ኅብረቱ፣ የተጠያቂነት ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ በመፍትሔነት ካስቀመጣቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል፣ “መንግሥታዊ አወቃቀሩን ወደ ፕሬዚዳንታዊ መንግሥት መቀየር” የሚል እንደሚገኝበት፣ አቶ መስዑድ አክለው ተናግረዋል።

በፍርድ ቤቶች እና በሕግ አውጪዎች መካከል በተጨባጭ እየስተዋለ ያለው የሥልጣን ሚዛን፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን እንደሚፃረር መገምገማቸውን ያነሡት አቶ መስዑድ፣ ተቃርኖው በአጀንዳነት እንዲታይ ማካተታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚኽም ረገድ በኅብረቱ የቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ በባለሞያዎች እና በምሁራን በደንብ ቢታይ፣ በተለይ በመንግሥት ይፈጸማሉ ለሚባሉ የመብቶች ጥሰቶች መፍትሔ እንደሚያመጣ፣ ኅብረቱ እምነት እንዳለው አቶ መስዑድ ተናግረዋል፡፡

የአናሳ ማኅበረሰብ ጥበቃ፣ ኅብረቱ ለምክክር የለየው ሌላው ቁልፍ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ሌላውም፣ የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ሲኾን፣ ሁለቱ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ላሉ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ግጭቶች መንሥኤ እንደኾኑ ተመልክቷል፡፡

እንደ ኅብረቱ አገላለጽ፣ “ይኼ የእኔ መሬት ነው፤ ይኼ የእኔ ክልል ነው፤ ከክልሌ ውጣ፤” በሚል በርካታ መፈናቀሎች እና ግጭቶች ሲፈጠሩ ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል፣ ከኅዳጣን ብሔረሰቦች ጥበቃ ጋራ ሊገናኝ እንደሚችሉ ያመለከታቸው ግጭቶቹ፣ አሳታፊ ፖለቲካዊ ሒደት እና የውሳኔ አሰጣጥ ካለመኖር ጋራ እንደሚያያዙ አስረድቷል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነቱም

ጉዳይ ከዚኹ ጋራ ተያይዞ የሚታይ እንደኾነ ኅብረቱ ገልጾ፣ እንደ አጀንዳ ቢያዝ፣ የመብቶች ጥሰቶቹ እንዲቀንሱ አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ ብሏል፡፡

የሲቪል ማኅበራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ ለማኅበራቱ የሚደረገው ጥበቃ ጉዳይም ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ የምክክር አጀንዳዎች መካከል መሆን እንዳለበት ኅብረቱ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በምክክር ሒደቱ ከፍተኛ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሳሰበው ኅብረቱ፣ የምክክር ኮሚሽኑ በተለየ መልኩ አመቺ ኹኔታን መፍጠር እንዳለበት አመልክቷል፡፡

ኅብረቱ፣ በዛሬው መድረክ ላይ፣ አጀንዳዎቹን፣ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች መካከል አንዷ ለኾኑት ወሮ. ብሌን ገብረ መድኅን ሲያቀርብ፣ ሌሎችም አካላት አጀንዳዎችን የማቅረብ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉበት ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል፡፡

ቀደም ሲል፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽንና የሴቶች ጥምረት ለሀገራዊ ምክክር፣ የበኩላቸውን አጀንዳዎች እንዳቀረቡ ያወሱት ወሮ. ብሌን፣ በዛሬው ዕለት በተደራጀ መንገድ ያዘጋጀውን አበርክቶውን ያስረከበው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት፣ ሦስተኛው የአጀንዳ ግብአት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በኮሚሽኑ ቢሮ በአካል ተገኝቶ የአጀንዳ ሐሳቦችን በተዘጋጀው ሣጥን ውስጥ ከማስገባት ጀምሮ፣ በኢሜይል እና በፖስታ መላክም እንደሚቻል ወሮ. ብሌን ጠቁመው፣ “የሐሳብ አካታችነትን ከማረጋገጥ አንጻር መሰል ጥረቶች እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአጀንዳዎቹ እና በምክክር ኮሚሽኑ ተግባራት ዙሪያ፣ በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ውይይት አድርገዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG