በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከአጎራባች ሀገራት የሚገባ የበረሓ አንበጣ ወረርሽኝ ያሰጋት ኤርትራ የመከላከል ጥሪ አደረገች


ከአጎራባች ሀገራት የሚገባ የበረሓ አንበጣ ወረርሽኝ ያሰጋት ኤርትራ የመከላከል ጥሪ አደረገች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:29 0:00

በኤርትራ፣ ጥሩ እና ሰፊ ሽፋን ነበረው የተባለው የባሕር ክረምት መውጣቱን ተከትሎ፣ በሰሜናዊ ቀይ ባሕር ሪጅን የበረሓ አንበጣ ወረርሽኝ እንደተከሠተ ያስታወቀው የግብርና ሚኒስቴር፣ በአኹኑ ወቅት በስፋት እየተስፋፋ እንደኾነ አስታወቀ።

ከኤርትራ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ምሥራቃዊ ዝቕተኛ ቦታዎች የተከሠተው ወረርሽኝ፣ ብዙም እንደማያሰጋ የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ ዋናው ስጋት፥ ከጎረቤት ሀገር ሱዳንና የመን ወደ ኤርትራ ሊፈልስ የሚችለው መንጋ እንደኾነ ኣመልክቷል።

በኤርትራ የሰሜናዊ ቀይ ባሕር ሪጅን፣ የበረሓ አንበጣ ወረርሽኝ እንደተከሠተ ያስታወቀው የኤርትራ ግብርና ሚኒስቴር፥ የመንግሥት አካላት፣ የመከላከያ ኀይሉ እና ሕዝቡ፣ ኹኔታውን በንቃት እንዲከታተሉና ወረርሽኙን ለመግታትም ዝግጁ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ያለንበት ወቅት፣ በኤርትራ ሰፊ የቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢ፣ ኢ-መደበኛ የክረምት ዝናም የሚከሠትበት እንደኾነ የግብርና ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፣ ይህም፣ አንበጣው እንዲፈለፈል ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥረለትና የወረርሽኙን ደረጃ አስጊ እንደሚያደርገው አሳስቧል፡፡

ካለፈው ኅዳር እና ታኅሣሥ ወር ጀምሮ፣ የአንበጣውን መፈልፈል የመቆጣጠር ሥራ ሲካሔድ እንደቆየ የጠቀሰው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፣ በዚኽም፣ “በሦስት የሰሜናዊ ቀይ ባሕር ሪጂንና በአንድ የደቡባዊ ቀይ ባሕር ሪጅን ወረዳዎች፣ በጠቅላላው በ18ሺሕ ሄክታር ላይ የታየ የአንበጣ መንጋ በቁጥጥር ሥር ውሏል፤” ብሏል፡፡ አኹንም፣ የቁጥጥር ሥራው በስፋት እንደቀጠለ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም፣ በጎረቤት ሱዳንና በየመን፣ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ የበረሓ አንበጣ በስፋት እየታየ እንደኾነና መንጋው ወደ ኤርትራ ሊፈልስ እንደሚችል ጠቁሞ፣ ሕዝቡ እና የመከላከያ ኀይሉ ኹኔታውን በንቃት እንዲከታተሉና ወረርሽኙን ለመግታት እንዲዘጋጁ አሳስቧል።

XS
SM
MD
LG