በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ገጣሚ በላይ በቀለ ያለበት ሳይታወቅና ያለፍርድ ለወራት እንደታሰረ ጠበቃው ተናገሩ


ገጣሚ በላይ በቀለ ያለበት ሳይታወቅና ያለፍርድ ለወራት እንደታሰረ ጠበቃው ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:37 0:00

የታሰረበት ቦታም ለረዥም ጊዜ ሳይታወቅ እንደቆየ የተናገሩት ጠበቃው አቶ ብሩክ ደረጀ፣ በአኹኑ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከቤተሰቦቹ ጋራ በመኾን፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር የአቤቱታ ደብዳቤ እንዳቀረቡም፣ ጠበቃው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከታላቁ ሩጫ ጋራ በተገናኘ ተይዘው በአንድ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ቁጥር 24 መድረሱንና እስከ አኹን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

በልዩ ልዩ የብዙኀን መድረኮች እና የማኅበራዊ ትስስር ገጾች፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ይዘት ያላቸውን ግጥሞች በማቅረብ የሚታወቀው ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ፣ በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለረዥም ጊዜ ያለበት ሳይታወቅ ተሰውሮ እንደቆየ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ብሩክ ደረጀ፣ በአኹኑ ወቅት፣ በባሕር ዳር ከተማ ታስሮ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ገጣሚው፣ እስከ አኹን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበም አመልክተዋል፣ “በወቅቱ፣ በዐዲስ አበባ ባሉ የጸጥታ መዋቅሮች ለማፈላለግ ሞክረን ልናገኘው አልቻልንም፡፡ በሕይወት መኖሩንና ባሕር ዳር ከተማ እንደሚገኝ በወሬ ወሬ ካወቅን አንድ ወር አካባቢ ቢኾነው ነው፡፡ በወባ በሽታ በጣም ታሞ ነበር፡፡ የኩላሊት ጠጠር ሕመምም እንዳለበት ከቤተሰቦቹ ሰምቻለኹ፡፡ እስከ አኹን ቤተሰብም ጠበቃም አያገኘውም፤ ወደ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡” ብለዋል።

ከገጣሚ በላይ ቤተሰቦች ጋራ ኾነው፣ አያያዙን የሚቃወምና የተፋጠነ ፍትሕን የሚጠይቅ የአቤቱታ ደብዳቤ፣ በዛሬው ዕለት ለፍትሕ ሚኒስቴር እንዳስገቡ፣ ያመለከተቱት ጠበቃ ብሩክ፤ “ወንጀል ከተገኘበት በምርመራ ተጣርቶ ክስ እንዲመሠረትና ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ፣ በዚኹ ጊዜም ቤተሰቦቹንና ጠበቃውን የማግኘት መብቱ እንዲጠበቅና ወደ ዐዲስ አበባ እንዲዛወር ጠይቀናል፡፡ በላይ ከታሰረ አራት ወራት ኾኖታል፡፡ ያጠፋው ካለ እስከ አኹን ፍትሕ ማግኘት፣ ከሌለም በነጻ መለቀቅ ነበረበት፤ ኹለቱም እየኾነ አይደለም፡፡” ብለዋል።

ለፍትሕ ሚኒስቴር የገባውና የአሜሪካ ድምፅ የተመለከተው የአቤቱታ ደብዳቤ፣ በላይ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኝ አሊያም በነጻ እንዲለቀቅ ያመለክታል፤ ቤተሰቦቹንና ጠበቃውንም ለማግኘት እንዲችልና ሕክምናም እንዲደረግለት ይጠይቃል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ 23ኛው ዙር “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” በተካሔደበት ውድድር ላይ ከተሰማው ተቃውሞ ጋራ በተገናኘ፣ ከኹነቱ ማግስት ኅዳር 10 ቀን ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው፣ በዐዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ታሳሪዎች ቁጥር 24 እንደደረሰና እስከ አኹን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል፡፡

“ከተያዙ አንድ ወር ሊኾናቸው ነው፡፡ እስከ አኹን ፍርድ ቤትም አልቀረቡም፡፡ በዛሬው ዕለትም አላዛርንና ቶማስን አግኝቻቸዋለኹ፡፡ ሓላፊዎች እንዳነጋገሯቸውና እነርሱም፣ ‘ምንም የሠራነው የሚያስጠይቀን ነገር የለም፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች እና ተማሪዎችም ነን፤ እንዳሏቸውና ቆዩ ከመባላቸው በቀር ሌላ የተባሉት ምንም ነገር እንደሌለ ገልጸውልኛል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ይለቁናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነግረውኛል፡፡”

ከታሳሪ የቤተሰብ አባላት መካከል፣ በማኅበራዊ የቪዲዮ መገናኛ አውታሮች፣ አዝናኝ ቪዲዮዎችን በማጋራት የሚታወቀው የአላዛር ታላቅ ወንድም ጆርጅ ወልደ ማርያም፣ አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡

“አኹንም፣ ማዕከላዊ ወይም ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው ያሉት፤ ፍርድ ቤትም አልቀረቡም፡፡ ማንን ማናገር እንዳለብን አላወቅንም፡፡ ሓላፊዎችን አግኝተን ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ብንሔድም ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ይሉናል፡፡ ወይ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ አልተባሉ ወይ ነጻ ናቸው ተብለው አልተለቀቁ፤ በጣም ተጨናንቀናል፡፡”

በታሳሪዎቹ ጉዳይ ላይ፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

ኾኖም ኢሰመኮ፣ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ፣ ከአስቸኳይ ዐዋጅ ጋራ በተገናኘ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎች፣ ምንም እንኳን እንደወትሮው በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ባይቀርቡም፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅ አሳስቦ ነበር፡፡

XS
SM
MD
LG