የዴንማርክ ፖሊስ “የሽብር ጥቃት ለማድረስ በመዘጋጀት ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ ባካሄድነው ዘመቻ በርካታ ሰዎችን አስረናል” አስታወቀ።
ሰዎቹ የታሰሩት ዛሬ ሐሙስ ማለዳ በበርካታ የዴንማርክ አካባቢዎች በተደረገ “የተቀናጀ እንቅስቃሴ” መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬድሪክሰን በብረስልስ በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት ጉባዔ ባደረጉት ንግግር ላይ “ይህ በጣም አሳሳቢ ነው፣ እንዳለመታደል ሆኖ ዴንማርክ ውስጥ ያለንበትን ሁኔታ ያሳያል” ማለታቸውን የአሶሲየትድ ዘገባ አመልክቷል፡፡
"ሁኔታው እጅግ አስጊ መሆኑን ሁለቱም የዴንማርክ የደህንነት ተቋማት መናገራቸው በጣም እውነት ነው" ያሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ “ከእስራኤል እና ጋዛ ጋር በተገናኘ ግጭቱን ወደ ሌላ የዓለም ክፍል፣ ወደ ዴንማርክ ማህበረሰብ የሚወስድ ሰው መኖሩ በፍፁም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዴንማርክ ያለው የሽብር ስጋት ደረጃ አራት የተሰጠው ሲሆን በከፍተኝነቱ ከእስከዛሬዎቹ ሁለተኛው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት የአገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ይልቫ ጆሃንሰን በእስራኤል እና በፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ጦርነት ምክንያት በዚህ የገና በዓል ወቅት አውሮፓ “ትልቅ የሽብር ጥቃቶች” ሊያገጥሟት ይችላል” በማለት አስጠንቅቀዋል ።
እ.ኤ.አ. ባለፈው 2022 ዓመተ ምሕረት በሐምሌ ወር አንድ ታጣቂ ከኮፐንሃገን ወጣ ብሎ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ውስጥ ሶስት ሰዎችን ገድሎ ሰባት ሰዎች ማቁሰሉ ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2015ም የ22 ዓመቱ ዴንማርካዊ ሙስሊም ታጣቂ፣ ኮፐንሃገን ውስጥ በንግግር ነጻነት ጉዳይ ዝግጅት እና በአይሁድ ምኩራብ ውስጥ ጥቃት አድርሶ ሁለት ሰዎችን ሲገድል አምስት ሰዎች ማቁሰሉ ይታወሳል፡፡
ጥቂት የፀረ እስልምና አቀንቃኞች ቁርአንን በአደባባይ ማጉደፋቸው፣ በሙስሊም ሀገራት ቁጣ የተሞላበት ህዝባዊ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ በዚህ ወር መጀመሪያ የዴንማርክ ምክር ቤት ማናቸውንም ቅዱስ መጽሀፍ ክብር ማዋረድ ህገ ወጥ መሆኑን የሚደነግግ ህግ አጽድቋል ፡፡
መድረክ / ፎረም