የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በሚመለከት ያቀዱት እቅድ ግቡ እንዳልተቀየረ ተናገሩ። እቅዱ እስከሚሳካም ምንም ሰላም እንደማይኖር ተናገሩ።
የሩሲያው መሪ ይህንን የተናገሩት የተያዘውን የአውሮፓውያን ዓመት መገባደድ ምክንያት በማድረግ ዛሬ ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ለ24 ዓመታት ሥልጣን ላይ ያሉት እና በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ እንደገና እንደሚወዳደሩ ያስታወቁት የሩስያው ፕሬዚደንት፣ በማዕከላዊ ሞስኮ ከሚገኘው አዳራሽ ሲደርሱ በጭብጨባ የታጀበ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ፕሬዚደንቱ በጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ፤ የሀገሪቱ ዜጎች ጥያቄያቸውን በስልክ ለማቅረብ በተሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ጠይቀዋል። ጠያቂዎቹ ጥያቄዎቻቸውን ለሁለት ሣምንታት በስልክ ሲያስመዘግቡ መቆየታቸውም ተነግሯል።
የዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ የውጪ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን ማነጋገር በእጅጉ የቀነሱት ፑቲን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምዕራባውያን ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ሊገጥማቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ዩክሬንን "ከናዚ ርዕዮተ ዓለም ማጽዳት፣ ከወታደራዊ ኃይል ነጻ ማድረግና እና ገለልተኛ አቋም ማስያዝ” ግባችን እንዳለ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
ፑቲን እ.ኤ.አ. የካቲት 2022 ዓም ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን በላኩበትን ዕለት ዓላማቸው ይህ መሆኑን ማወጃቸው ይታወሳል፡፡የዩክሬን መንግሥት “አክራሪ ብሔርተኞች እና የናዚ ርዕዮተ ዓለምን ለማንሰራራት በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ወርሰውታል” በማለት ሩሲያ ትወነጅላለች። ክሱን ዩክሬን እና ምዕራቡ ዓለም አጣጥለውታል።
ዩክሬን “ገለልተኝነቷን እንድትጠብቅ - እና የኔቶ ኅብረትን እንዳትቀላቀል” የጠየቁት ፑቲን “ዓላማዎቻችንን ስናሳካ ሰላም ይኖራል” ብለዋል፡፡
ጦርነቱን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ክሬምሊን እነዚህ በጥቅሉ የተቀመጡ ግቦች እስኪሳኩ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻችን ይቀጥላል በማለት በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፡፡
ስለ ሞስኮው ወታደራዊ ዘመቻ በዝርዝር በመናገር የማይታወቁት ፑቲን “ወደ ዩክሬን የዘመቱት 244,000 ወታደሮቻችን አሁንም ጦር ሜዳው ላይ ናቸው” ብለው፣ “ለሁለተኛ ዙር የተጠባባቂ ጦር አባላትን መጥራት አያስፈልገንም” በማለት አጣጥለዋል።
የሆነ ሆኖ ፕሬዚደንቱ የመደበኛው የጦር ሠራዊት አባላትን ጨምሮ ምን ያህል ወታደሮች ዩክሬን እንዳሉ በዝርዝር አልተናገሩም።
ፑቲን እ.ኤ.አ. ባለፈው 2022 ዓመተ ምሕረት መስከረም ወር ውስጥ በዩክሬን ያሰማሩትን ኃይል ለማጎልበት በከፊል ተጨማሪ ሠራዊት እንዲጠራ ማዘዛቸው ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
በዛሬው ጋዜጣዊ ጉባዔያቸው “ባሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በየቀኑ 1,500 የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል እየተመለመሉ ስለሆነ ተጠባባቂ ኃይል መጥራት አያስፈልገንም” ያሉት ፕሬዚደንቱ “እስከ ትናንት ረቡዕ ምሽት በአጠቃላይ 486,000 ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ጋር የቅጥር ውል ተፈራረመዋል” ብለዋል፡፡
ከዩክሬን ጦርነት በተጨማሪ የኢኮኖሚው እና የማህበራዊ አገልግሎቶች ጉዳይ በጋዜጣዊ ጉባኤው ላይ እንደሚነሳ የሩሲያ መንግሥት ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ፑቲን ባለፈው ዓመት የተለመደውን ከዜጎች በስልክ የሚቀርብ ጥያቄና መልስም ሆነ ጋዜጣዊ ጉባኤ አላካሄዱም፡፡
መድረክ / ፎረም