ዩክሬን፣ ከሩሲያ ጋራ ለገባችበት ጦርነት መርጃ የሚውል ገንዘብ ሴኔቱ እንዲያጸድቅላቸው እያግባቡ ያሉት የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ ከሪፐብሊካኑ ወገን በመጣውና በሜክሲኮ ድንበር በኩል የሚገቡ ፍልሰተኞችን ለመግታት በቀረበው ሐሳብ ላይ ተስማምተዋል።
ኮንግረሱ፣ መጪውን ዐውደ ዓመት አስመልክቶ፣ በዚኽ ሳምንት መጨረሻ ለዕረፍት የሚበተን ቢኾንም፣ አንዳንድ እንደራሴዎች ግን ስምምነቱን ለመቋጨት ዋሽንግተን እንደሚቀሩ፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
ኋይት ሐውስ፣ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ወሳኝ ከኾኑ የሴኔት አባላት ጋራ እየተደራደረ ሲኾን፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌሃንድሮ ማዮርጋን የጨመረው ተደራዳሪ ቡድን፣ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ባይደርስም፣ በትላንቱ የኮንግረስ ውሎ መልካም ውጤቶችን አግኝቷል፤ ተብሏል።
የፍልሰተኞች መብት ተከራካሪዎች እና በፕሬዚዳንቱ የዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ ያሉ አባላት፣ ለድርድር በቀረቡትና ፍልሰተኞችን በተመለከቱ ፖሊሲዎች ላይ ተቃውሞ አላቸው።
በፕሬዚዳንት ባይደን የቀረበውንና ለዩክሬንና ለእስራኤል፣ እንዲሁም ለሌሎች የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች የሚውል የ110 ቢሊዮን ዶላር በጀት ለማጽደቅ ምክር ቤቱ ያለው ጊዜ እጅግ አጭር ነው። ሪፐብሊካኖቹ፣ የድንበር ሕጉን የሚያጠብቅ ደንብም አብሮ መውጣት አለበት፤ በሚል፣ በጀቱ እንዳይጽድቅ አግደዋል ቆይተዋል።
መድረክ / ፎረም