ዛሬ እሁድ በጋዛ ሰርጥ ውጊያው በቀጠለበት ሁኔታ፣ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር፣ እስራኤል በጋዛ ላይ በምትፈጽመው ጥቃት ፍልስጤማውያን ሲቪሎችን ከሞት እንድትጠብቅ የሚያሰማውን ጥሪ ቀጥሏል።
ለሰባት ቀናት የነበረው ተኩስ ማቆም ከትናንት በስቲያ ዓርብ ማክተሙን ተከትሎ፣ እስራኤል በደቡብ ጋዛ የሚገኘውን የካን ዩኒስ ከተማ ካለማቋረጥ በመደብደብ ላይ ነች፡፡
እንደ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ ከሆነ፣ እስራኤል ፍልስጤማውያን ለቀው እንዲወጡ የምትጠይቀውን አካባቢ፣ የሃማስ መሪዎች ተደብቀውበታል ወዳለችው ወደ ደቡብ ጋዛም በማስፋት፣ ድብደባዋን ቀጥላለች፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታንያሁ ትናንት እንዳስጠነቀቁት፣ በሐማስ የተያዙት ታጋቾች እስኪለቀቁ እና ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ እስከሚደመሰስ ድረስ ጥቃቱ ይቀጥላል።
“ከባዱ ጦርነት ከፊታችን ይገኛል” ሲሉ ተደምጠዋል ነታን ያሁ።
“እጅግ ብዙ ንጹሃን ፍልስጤማውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሲቪሎች ሰቆቃ እና ከጋዛ የሚወጡ ምስሎች እና ቪዲዮዎች የሚረብሹ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል በዱባይ በሚካሄደው የአየር ንብረት (ኮፕ28) ጉባኤ ላይ በመሳታፈ ላይ ያሉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሃሪስ።
“ለእስራኤል ደህንነት ያለን ድጋፍ ለድርድር የማይቀርብ ነው” ያሉት የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን፣ እስራኤል ለሲቪሎች ጥበቃ የማታደርግ ከሆነ፣ ድጋፋቸው ችግር እንደሚገጥመው በግል እንዳስጠነቀቁ ተናግረዋል።
ዓርብ ተኩስ ማቆሙ ካበቃ ወዲህ ብቻ ቢያንስ 200 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ የሞቱት ቁጥር 15ሺሕ 200 እንደደረሰና፣ 40ሺሕ ደግሞ እንደቆሰሉ በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም