የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ እና የላይቤሪያው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዊሃ በድጋሚ በተደረገው ተቀራራቢ ፕሬዝደንታዊ ፎክክር በተቃዋሚው መሪ ጆሴፍ ቦአካይ መሸነፋቸውን አምነዋል።
“ከግል ፍላጎት ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደሚያው ሰዓት ነው” ሲሉ ጆርጅ ዊሃ ተናግረዋል።
በመጠናቀቅ ላይ ባለው ድምጽ ቆጠራ፣ ጆሴፍ ቦአካይ 51 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ታውቋል።
“ዛሬ ምሽት በወጣው ውጤት መሠረት፣ የመጨረሻው ባይሆንም፣ ቦአካይ እየመሩን ነው፣ ከዛ የሚበልጥ ድምጽ ማግኘት አንችልም” ሲሉ ዊሃ ትናንት ምሽት በአገሪቱ ብሔራዊ ራዲዮ መናገራቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
“ፓርቲዬ ሲዲሲ ምርጫውን ተሸንፏል፣ ላይቤሪያ ግን አሸንፋለች” ብለዋል ዊሃ።
የ78 ዓመቱ ጆሴፍ ቦአካይ ከስድስት ዓመታት በፊት በተደረገው ምርጫ በጆርጅ ዊሃ ተሸንፈው ነበር።
ማክሰኞ በተደርገው የድጋሚ ምርጫ ከተሰጠው ድምጽ 99.5 በመቶ መቆጠሩን እና ጆሴፍ ቦአካይ በ28 ሺሕ ድምጽ እየመሩ እንደሆነ የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም