በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከጋዛው ሺፋ ሆስፒታል ታካሚዎች እና ሠራተኞች ለቀው ወጡ


አል ሺፋ ሆስፒታል (ፎቶ ፋይል ሮይተርስ)
አል ሺፋ ሆስፒታል (ፎቶ ፋይል ሮይተርስ)

እስራኤል ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ያሉ ታካሚዎች እና ሠራተኞች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አላስተላለፍኩም ብትልም፣ ከጥቂት ታካሚዎች እና ሠራተኞች በስተቀር ሌሎች ለቀው መውጣታቸው ተዘግቧል።

ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ሰዎች ከሆስፒታሉ እንዲወጡ መርዳት እንደምትሻ ለሆስፒታሉ ዲሬክተር መግለጿን እስራኤል አስታውቃለች፡፡

የኤኤፍፒ ዜና ወኪል በበኩሉ እስራኤል ሰዎች ከሆስፒታሉ ለቀው እንዲወጡ የአንድ ሰዓት ግዜ ብቻ ሰጥታ እንደነበር ዘግቧል።

ሁለቱ ተቃራኒ ሪፖርቶች እየተሰሙ ባለበት ሁኔታ፤ ታካሚዎች፣ ሠራተኞች እና በሆስፒታሉ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች ዛሬ ቅዳሜ ጥለው መውጣታቸው ተነግሯል።

መንቀሳቀስ የማይችሉት ታካሚዎች ብቻ ከጥቂት ሠራተኞች ጋር መቅረታቸው ታውቋል።

በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ከሆነው ሺፋ ሆስፒታል ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አለማስተላለፉን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል።

በሆስፒታሉ ምድር ሥር የሐማስ ታጣቂዎች ተደብቀዋል ስትል እስራኤል ትከሳለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፍልስጤማውያኑ ፕሬዝደንት ሞሃሙድ አባስ ፋታህ ፓርቲ ውስጥ የነበሩ አምስት ተዋጊዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን የፍልስጤማውያን ቀይ ጨረቃ እና የፋታህ ፓርቲ ምንጮች አስታውቀዋል። በዌስት ባንክ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ያልተለመደ መሆኑ ተነግሯል።

በሌላ በኩል እስራኤል በሀማስ ላይ በምታደርገው ጦርነት ምክንያት የጀርመኑ እና የቱርክ መሪዎች ኃይለ ቃል ተለዋውጠዋል። የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት ሲሉ፣ የቱርኩ ፕሬዝደንት ረቸፕ ታይፕ ኤርዶዋን በበኩላቸው እስራኤል የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም ጠይቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG