የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ፣ ፖለቲካዊ ጫና እንደበረታበት የገለጸ አንድ ጥናት፣ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በየመሥሪያ ቤቱ ለሚታየው የመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት እንደኾነ አመለከተ፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተዘጋጀ አንድ የውይይት መድረክ ላይ፣ በዘርፉ ያካሔዱትን ጥናት ይፋ ያደረጉት፣ የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶር. ብርሃኑ ተመስገን፣ የአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ፥ ከፖለቲካ ነፃ ኾኖ፣ ብቃትንና ችሎታን መሠረት ባደረገ አሠራር መመራት ሲገባው፣ “ይህ ግን እየኾነ አይደለም፤” ብለዋል፡፡
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በውድድር ሊያዙ የሚገባቸው የሥራ መደቦች፣ በፖለቲካዊ መስፈርት ሹመት እንደሚካሔድባቸው የጠቀሱት ባለሞያው፣ ይህ ደግሞ ለአገልግሎት አሰጣጡ መጓደል ምክንያት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ፣ የተለያዩ ችግሮች እንደሚታዩና አገልግሎታቸው በብልሹ አሠራር የተተበተበ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።