በጋዛ ከተማ፣ የእስራኤል ኃይሎች ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ ዛሬ ሐሙስ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የምድርና የአየር ድብደባ ቀጥላለች፡፡
በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ሲቪሎች ከተማውን እየለቀቁ ሲሆን፣ እስራኤል ዋና ትኩረቴ ነው ከምትለው የሐማስ ታጣቂዎች ጋር የምታደርገውን ውጊያ መቀጠሏን ገልጻለች፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 50,000 ፍልስጤማውያን ወደ ደቡባዊ ጋዛ መሰደዳቸውንና ካለፈው እሁድ ጀምሮ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በድምሩ 72 ሺህ መድረሱን አስታውቋል፡፡
የእስራኤል ኃይሎች ተፈናቃዮቹ አካባቢውን ለቀው የሚወጡበትን መተላለፊያ መንገድ ለአራት ሰዓታት ከፍተው እንደነበርም ተመልክቷል፡፡
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ጥቃት ከ10,500 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ገልጿል።
ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ሚኒስቴሩ ቁጥሮች ቀደም ባሉት ጊዜያት አስተማማኝ መሆናቸውን ቢገልጽም እነዚያን ቁጥሮች አሁን በተናጥል የሚያረጋግጡበት ምንም መንገድ አለመኖሩ ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ ሁኔታው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ተላላፊ በሽታዎች ሊስፋፉ እንደሚችሉ አስጠነቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ የእስራኤል ድርጊትም ሆነ የሐማስ ጥቃት የጦር ወንጀሎች ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
በዓለም የበለጸጉ የቡድን 7 አባል አገራት የእስራኤልን ራስን የመከላከል እርምጃ የሚደግፉ መሆኑን ገልጸው ለፍልስጤማውያን ሲቪሎች እርዳታ እንዲደርስ ግን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
መድረክ / ፎረም