በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋዛ ጦርነት "ረጅም እና አስቸጋሪ" እንደሚሆን ኔታንያሁ ተናገሩ


እስራኤል በጋዛ ላይ በፈፀመችው የአየር ድብደባ የፈራረሱ ሕንፃዎች፤ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም
እስራኤል በጋዛ ላይ በፈፀመችው የአየር ድብደባ የፈራረሱ ሕንፃዎች፤ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም

እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ አስገብታ፣ የምድር፣ የአየር እና ባየህር ላይ ጥቃቶችን እያካሄደች መሆኑን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ዛሬ ጥቅምት 17 2016 ዓ.ም አስታወቁ። የጋዛ ጦርነት ወደ "ሁለተኛ ምዕራፍ" ተሸጋግሯል ብለዋል።

ጦርነቱን ለሀገር ህልውና እንደሚደረግ ትግል አድርገው የገለፁት ኔታንያሁ፣ ሰፊ የመሬት ወረራ በሚካሄድበት ወቅት ጥቃቱ እየጠነከረ እንደሚሄድ አስጠንቅቀዋል።

"አንድ ሀገር ሁለት አማራጮችን ብቻ የሚጋፈጥበት ጊዜ አለ፣ ወይ ማድረግ ወይ መሞት" ያሉት ኔታንያሁ፣ "እኛ አሁን ከፊታችን የሚጠብቀን ይህ ፈተና ነው። እኛ አሸናፊዎች ኾነን እንደሚያበቃ ደግሞ ጥርጥር የለኝም። ያንን እናደርጋለን፣ አሸናፊዎችም እንሆናለን" ብለዋል።
የጋዛ ነዋሪዎች እስከዛሬ በጦርነቱ ከተካሄደው ጥቃት እጅግ የከፋ ሲሉ የገለፁት የቦምብ ጥቃት በግዛቱ ውስጥ የነበረውን አብዛኛውን ግንኙነቶች ያቋረጠ ሲሆን፣ በታጣቂዎች ከበባ መሃል የሚኖሩትን 2.3 ሚሊየን ነዋሪዎች ከቀሪው ዓለም ለያይቷቸዋል።
የእስራኤል ጦር አብዛኞቹ ከድንበር አቅራቢያ ያሉ የሚመስሉ ታንኮች፣ በሰልፍ ክፍት ወደ ሆኑ የጋዛ አካባቢዎች በቀስታ ሲንቀሳቀሱ የሚያሳዩ ደብዛዛ ምስሎችን የለቀቀ ሲሆን፣ የጦር አሮፕላኖች በደርዘን የሚቆጠሩ የሐማስ መተላለፊያ ዋሻዎችን እና የመሬት ስር ምሽጎችን በቦምብ መደብደባቸውን አስታውቋል።
ከሦስት ሳምንት በፊት በእስራኤል ውስጥ ደሞ አፋሳሽ ወረራ ከተካሄደ በኃላ፣ እስራኤል ግዛቱን የሚያስተዳድረውን ቡድን ለመደምሰስ በምታደርገው ዘመቻ፣ ከመሬት በታች የሚገኙ ስፍራዎች የእስራኤል ቁልፍ ኢላማዎቿ ናቸው።
እየተባባሰ የሄደው ጦርነት፣ መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ አቅራቢያ ወደሚገኙ የእስራኤል ከተሞች በመግባት ሰላማዊ ዜጎችን እና ወታደሮችን በገደሉበት ወቅት የወሰዷቸውን በደርዘን የሚቆጠሩ ታጋቾችን እንዲያስለቅቅ፣ በእስራኤል መንግሥት ላይ የሚደረገውን የሀገር ውስጥ ጫና አባብሷል።
በአይሁዶች ታላቅ በዓል እለት የደረሰው ጥቃት፣ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ወደ ቀሪው መካከለኛው ምስራቅ ሊሻገር ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል።
ተስፋ የቆረጡ የታጋች ቤተሰብ አባላት ቅዳሜ እለት ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው፣ በእስራኤል ለታሰሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች ልውውጥ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል። ሀሳቡ የቀረበው ጋዛ ከሚገኝ አንድ ከፍተኛ የሐማስ አመራር ነው።
ኔታንያሁ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እስራኤል ታጋቾችን በሙሉ ለማስመለስ ቆርጣ መነሳቷን የገለፁ ሲሆን፣ አሁን በመሬት የተጀመረው ወረራ "ለዚህ ተልዕኮ ይረዳናል" ብለዋል። እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች ሚስጥራዊ በመሆናቸውም ሁሉንም ነገር በግልፅ መናገር እንደማይችሉም ተናግረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ዛሬ ጥቅም 17/2016 ዓ.ም መግለጫ ሲሰጡ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ዛሬ ጥቅም 17/2016 ዓ.ም መግለጫ ሲሰጡ።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ይህ የጦርነቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ነው። ዓላማውም ግልፅ ነው። የሐማስን ወታደራዊ እና መንግሥታዊ አቅም ማጥፋት፣ ታጋቾችን ወደ ቤታቸው መመለስ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኔታንያሁ ለተኩስ አቁም ጥሪዎች ምላሽ ባይሰጡም፣ ክፍለ ዘመናት ያስቆጠረውን የአይሁዶች ታሪከ እና ወታደራዊ ግጭቶችን በማጣቀስ ባደረጉት ንግግር፣ የእስራኤል የወደፊት እጣ ፈንታ "በጠላት" ኃይሎች ላይ በሚኖረው ስኬት እንደሚወሰን በመግለፅ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አመለካከት ግልፅ አድርገዋል።
"ጀግኖች ወታደሮቻችን አንድ ታላቅ ግብ ነው ያላቸው፣ ገዳዩን ጠላታችንን ማጥፋት እና በምድራችን ላይ ያለንን ህልውና ማረጋገጥ። ሁልጊዜ "በፍፁም አይደገምም" እንላለን። "በፍፁም አይደገምም" አሁን ሆኗል።"
ኔታንያሁ አክለው፣ ከ1ሺህ 400 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የመስከረም 26 ጥቃት ጥልቅ ምርመራ እንደሚያስፈልገው የገለፁ ሲሆን፣ "እኔን ጨምሮ ሁሉም መልስ ይሰጥበታል" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ውስጥ በምድር ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ ቀስ በቀስ እያሰፋ መሄዱን ቢገልፅም፣ ሙሉ ለሙሉ ወረራ ብሎ ከመጥራት ግን ተቆጥቦ ቆይቷል። የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት የባሕር ኃይል ዋነ አዛዥ ዳንኤል ሀጋሪ "በነበረን የተቀናጀ እቅድ መሰረት የጦርነቱን ደረጃ ተከትለን እየቀጠልን ነው" ብለዋል።
ይህ አስተያየት ግዙፍ እና ከፍተኛ አቅምን ካሰባሰበ ጥቃት ይልቅ፣ ቀድሞ በተጠና መልኩ እየጨምረ መሄዱን የሚያሳይ ፍንጭ መሆኑን ጠቁሟል።
እስራኤል ዛሬ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም ጋዛ ሰርጥ ላይ ያደረገችውን የአየር ድብደባ ተከትሎ አካባቢው በእሳትና ጭስ ታፍኗል።
እስራኤል ዛሬ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም ጋዛ ሰርጥ ላይ ያደረገችውን የአየር ድብደባ ተከትሎ አካባቢው በእሳትና ጭስ ታፍኗል።
ጦርነቱ ገና ሲጀመር እስራኤል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ድንበር ላይ አሰባስባለች። እስካሁን በነበረው ጊዜም ወታደሮቿ አጫጭር የምሽት ወረራዎችን አካሂደው ወደ እስራኤል ተመልሰዋል ።
የእስራኤል ጥቃት እንዳለ ሆኖ፣ የፍልስጤም ታጣቂዎችም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሳቸውን ቀጥለዋል። አደጋ እንዳለ የሚገልፀው የማስጠንቀቂያ ደውልም ደቡብ እስራኤል ውስጥ በተከታታይ መሰማቱን ቀጥሏል።
ጦርነቱ ከተጀመረው ወዲህ በጋዛ ውስጥ የሞተው ሰው ቁጥር 7ሺህ ሰባት መቶ የደረሰው ሲሆን አርብ ምሽት ብቻ 377 ሰዎች መሞታቸው መመዝገቡን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል። አብዛኛው ህይወታቸው ያለፉት ሰዎችም ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸውን ገልጿል።
የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አሽራፍ አል-ቂድራ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "የግንኙነቶች መቆራረጥ የጤና መረቡን “ሙሉ በሙሉ ሽባ አድርጎታል" ብለዋል።
ነዋሪዎች አምቡላንሶችን የሚጠሩበት መንገድ የሌላቸው ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ቡድኖች የመድፍ እና የአየር ድብደባ የተካሄደባቸውን ስፍራዎች ድምፅ በመከተል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አክሎ 1 ሺህ 700 ሰዎች በፍርስራሾች መካከል መውጫ አጥተው እንደሚገኙ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም መስሪያ ቤቱ ከደረሰው ጥሪ የተነሳ ግምት መሆኑን አመልክቷል።
አንዳንድ ሲቪሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች፣ በባዶ እጃቸው ከፍርስራሾች መካከል አውጥተው በግል መኪናቸው ወይም በአህያ ጋሪ እየጫኑ ይወስዷቸዋል።
አንድ በአካባቢው የዜና ማሰራጫ የተላለፈ የቪዲዮ ምስል፣ ፍልስጤማውያን በህንፃ ፍርስራሹ አቧራ የተሸፈነ አንድ ቁስለኛ ይዘው መንገድ ላይ ሲሮጡ አሳይቷል። ቃሬዛውን በጭነት መኪና ውስጥ አስገብተው 'ሂድ! ሂድ!' እያሉ በመሃል አንድ ሰው "አምቡላንስ! አምቡላንስ!" እያለ ሲጮህም ይታያል።
አንዳንድ የጋዛ ነዋሪዎች ዘመዶቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ በእግራቸው ወይም በመኪና ይጓዛሉ። የስልክ አገልግሎት ከሚያገኙ ጥቂት ሰዎች አንዷ የሆነቸው፣ በማዕከላዊ ጋዛ የምትገኘው ጋዜጠኛ ሂንድ አል-ኩዳሪ ስለሁኔታው ስታስረዳ "ቦምብ በየቦታው ነው የሚጣለው፣ ህንፃው እየተንቀጠቀጠ ነበር" ትላለች።
"ማንንም ማግኘት አንችልም። ቤተሰቦቼ የት እንዳሉ አላውቅም።" እስራኤል ለምታደርሰው ጥቃት ኢላማዋ የሐማስ ታጣቂዎች እና መሰረተ ልማቶች መሆናቸውን ገልፃ፣ ታጣዊዎቹ በሲቪሊያኖች መካከል የሚቀሳቀሱ በመሆናቸው ለአደጋ አጋልጠዋቸዋል ትላለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG