በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታንዛኒያ ከዱባይ ኩባንያ ጋራ አወዛጋቢ የወደብ አስተዳደር ስምምነት ተፈራረመች


ታንዛኒያ ከዱባይ ኩባንያ ጋራ አወዛጋቢ የወደብ አስተዳደር ስምምነት ተፈራረመች
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:28 0:00

የታንዛኒያ መንግሥት፣ መቀመጫውን በዱባይ ካደረገው ዲፒ ወርልድ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክ ኩባንያ ጋራ የተፈራረመው የወደብ ስምምነት፣ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሥቷል፤ በደርዘን የሚቆጠሩ ተቺዎችም ለእስር ተዳርገዋል።

ታንዛኒያ፣ ከዲፒ ወርልድ ጋራ ስምምነት የፈጸመችው፣ ፕሬዚዳንቷ ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በተገኙበት ነው፡፡ ርእሰ ብሔሯ ሳሚያ ሱሉሁ፣ ከእርሳቸው በፊት እንደነበሩት ሟቹ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ፣ ተቃዋሚዎችንና ተቺዎችን በማፈን ቅሬታ ይቀርብባቸዋል።

የታንዛኒያ የወደቦች ባለሥልጣን ዲሬክተር ጀነራል፣ ፕላስዱስ ምቦሳ ስለ ስምምነቱ ሲያስረዱ፤ ዲፒ ወርልድ የሚያስተዳደረው፣ የአገሪቱን ጠቅላላ ወደብ ሳይኾን፣ በንግድ መዲናዋ በዳሬ ሰላም ከተማ የሚገኘውን፣ አራት የመርከብ ማራገፊያ ቦታዎችን ብቻ እንደኾነ ገልጸዋል። ለ30 ዓመታት የሚዘልቀው የውል ስምምነቱ፣ በየአምስት ዓመቱ እንደሚገመገምም ጠቁመዋል።

ተቃዋሚዎች እና የሲቪል ማኅበረሰቦች ግን፣ የታንዛኒያ ወደቦች፣ በውጪ የሎጂስቲክ ኩባንያ እንዲተዳደር መወሰኑን ተቃውመዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ፣ ርምጃው የወደብ ብቃትን እንደሚያሻሽልና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ አመልክቷል።

የታንዛኒያ ፓርላማ፣ እ.አ.አ ሰኔ 10 ቀን ያጸደቀው ይህ ስምምነት፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሥነሳቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ እስከ አሁን 22 ሰዎች እንደታሰሩ፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋም ሂዩማን ራይትስ ወች አስታውቋል። ተቋሙ፣ በነሐሴ ወር ባወጣው ሪፖርትም፣ ታንዛኒያ በነጻነት ሐሳብን የመግለጽ መብትንና የመቃወም መብትን እንድታከብር ጠይቆ ነበር።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

XS
SM
MD
LG