በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሐማስ-እስራኤል ግጭት ላይ የሚመክር ጉባኤ በካይሮ በመካሄድ ላይ ነው፤ ጉቴሬዥ ‘የሰብዓዊ ተኩስ አቁም’ እንዲደረግ ጠየቁ


በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ላይ በካይሮ በመደረግ ላይ ባለው ጉባኤ ተሳታፊ የሀገራት መሪዎች (ፎቶ ሮይተርስ ጥቅምት 21፣ 2023)
በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ላይ በካይሮ በመደረግ ላይ ባለው ጉባኤ ተሳታፊ የሀገራት መሪዎች (ፎቶ ሮይተርስ ጥቅምት 21፣ 2023)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሓፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዥ፣ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚካሄደው ግጭት የፈጠረው “አሰቃቂ ቅዠት” ብለው የገልጹት ሁኔታ እንዲያከትም እና ለሰብዓዊ ሥራ ሲባል ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።

ዋና ፀሓፊው ዛሬ ጥሪውን ያሰሙት በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ላይ በካይሮ በመደረግ ላይ ባለው ጉባኤ ላይ ነው።

ጉቴሬዥ እንዳሉት፣ በጋዛ ሰርጥ 2.4 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን “በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ” በመኖር ላይ ሲሆኑ፣ በሺሕ የሚቆጠሩት ሕይወታቸውን ሲያጡ ከሚሊዮን በላይ ተፈናቅለዋል ብለዋል።

በካይሮው ጉባኤ ላይ የአስተናጋጇ ግብፅ፣ የኢራቅ፣ የጆርዳን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ የጣሊያን እና የእስፔን መሪዎች እንዲሁም የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ተገኝተዋል።

“የተገናኘነው እጅግ ስቃይ ላይ ባለ እና ሌላ የገደል አፋፍ ላይ በሚገኝ ቀጠና ውስጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ጉቴሬዥ።

“የፍልስጤማውያኑ ቅሬታ ተገቢ ነው፤ ለ56 ዓመታት ግዛታቸው በእስራኤል ተይዟል። ቢሆንም ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውና እስራኤላውያንን ያሸበረው ጥቃት በምንም ዓይነት ምክንያት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል ጉቴሬዥ።

የግብፁ ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በበኩላቸው፤ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ላለው ግጭት ብቸኛ መፍትሄ “ፍትህ” ነው ብለዋል። “ፍልስጤማውያኑ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸው ተግባራዊ ሊሆን እና በመሬታቸው ላይ የራሳቸው ሉአላዊ ሀገር ሊኖራቸው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል አል ሲሲ።

የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ደግሞ፣ የሁለት ሀገራትን መፍትሄ አጽንኦት ሰጥተው በመናገር፣ እስራኤል የያዘችውን ግዛት ለቃ እንድትወጣ ጠይቀዋል። “ፍልስጤማውያኑ ለሁለተኛ ግዜ ከመሬታቸው ሊፈናቀሉ አይገባም ሲሉ” በእስራኤል መፈጠር ወቅት፣ 760 ሺሕ ፍልስጤማውያን የተበተኑበት ሁኔታ እንደገና እንደማይደገም ለመግለጽ፣ “የትም አንሄድም!” ሲሉ ሶሶት ግዜ ደጋግመው ለጉባኤው ተናግረዋል።

///

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG