በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን አሜሪካዊያን ከእሥራዔልና ከዩክሬን ጎን እንዲቆሙ ጠየቁ


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ ማምሻውን ከዋይት ሃውስ ቢሯቸው ለህዝባቸው በቀጥታ ንግግር ሲያደርጉ።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ ማምሻውን ከዋይት ሃውስ ቢሯቸው ለህዝባቸው በቀጥታ ንግግር ሲያደርጉ።

ዩክሬንና እሥራዔል እያካሄዱ ላሉት ጦርነቶች አሜሪካዊያን በገንዘብ መደገፋቸውን እንዲቀጥሉ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ ማምሻውን ከዋይት ሃውስ ቢሯቸው ለህዝባቸው በቀጥታ ባደረጉት ንግግር ጠይቀዋል።

ባይደን ሃማስንና የሩሲያውን ፑቲንን ያተካከሉበትን የምሽቱን ንግግር ያደረጉት የዋሺንግተን ወዳጅ ለሆነችው እሥራዔል ድጋፋቸውን ለማሳየት በጦርነቱ መካከል ካደረጉት የቴል አቪብ ጉብኝት በተመለሱ ማግሥት ነው።

አንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በጦርነት ውስጥ እሥራዔልን ሲጎበኝ የከትናንት በስተያው የባይደን ጉዞ የመጀመሪያ ሆኗል።

ፕሬዚዳንቱ ሁለቱም ጦርነቶች ውስጥ ሃማስና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ፈፅመዋል ያሏቸውን የከፉ ጥፋቶች ሲገልፁ “ሁለቱም የየጎረቤታቸውን ዴሞክራሲ ሙሉ በሙሉ ጠራርገው ለማጥፋት ይፈልጋሉ” ብለዋል።

“ሁለቱንም እንደሚያቆሙ” ባይደን ሲዝቱ “ሽብርተኞች ለሽብራቸው፣ አምባገነኖች ለሁከታቸው ዋጋ ሳይከፍሉ ሲቀሩ የሚፈጥሩት ትርምስ፣ ሞትና ውድመት እየበረታ እንደሚሄድ ታሪክ አስተምሮናል” ብለዋል።

ቁልፍ አጋሮችን ለመደገፍ የአሜሪካ ብሄራዊ ደኅንነት ጉዳይ መደበኛ ላልሆኑ የመንግሥት መርኃግብር ማስፈፀሚያ የሚውል የተጨማሪ ድጋፍ ጥያቄ ለተወካዮች ምክር ቤቱ እንደሚልኩ ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ የሚጠይቁትን ገንዘብ ልክ በዛሬው ንግግራቸውን ላይ ባይናገሩም የተለያዩ የዜና አውታሮች ግን መቶ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተመሳሳይ ዘገባዎችን ሲያወጡ ውለዋል።

ከአንድ ሺህ አራት መቶ በላይ ሰው ለተገደለበትና ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ደግሞ ለታገቱበት የመስከረም 26 የሃማስ ታጣቂ ቡድን ወረራ እሥራዔል እየሰጠች ላለችው ወታደራዊ ምላሽ ዩናይትድ ስቴትስ የማይናወጥ ድጋፏን እንደምሰጥ ባይደን በዚሁ ንግግራቸው አረጋግጠዋል።

እሥራዔል ለሃማስ ጥቃት ባካሄደቻቸው የአፀፋ የአየር ድብደባዎች ከሦስት ሺህ በላይ ህይወት መጥፋቱና ጋዛ ውስጥ አብዛኛው ፍልስጥዔማዊ አረብ የሆነ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው መፈናቀሉ ተዘግቧል።

ዩክሬንን በሚመለከት ዛሬ (ሃሙስ) ረፋድ ላይ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር መነጋገራቸውንም ገልፀው ለሃገሪቱ ሉዓላዊነት፣ የግዛት መጠበቅና የዴሞክራሲ መፃዒ ጊዜ የሚሰጡትን ድጋፍ በድጋሚ እንደሚያረጋግጡ ፕሬዚዳንት ባይደን ተናግረዋል።

(ከተጨማሪ ማብራሪያዎች ከምላሾችና ከትንታኔዎች ጋር እንመለሳለን።)

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG