በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቱሉ ምልኪ ከተማ ነዋሪዎች በመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ለዜጎች ደኅንነት ሓላፊነት የጎደለው” ግጭት እንደተማረሩ ገለጹ


በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወራ ጃርሶ ወረዳ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ለዜጎች ደኅንነት ሓላፊነት የጎደለው” ተደጋጋሚ የተኩስ ልውውጥ በሕዝብ መካከል እንደሚያደርጉ የገለጹ የቱሉ ምልኪ ከተማ ነዋሪዎች፣ በርካታ ንጹሐንን ለኅልፈት እየዳረገ ባለው ግጭት እንደተማረሩ ተናገሩ፡፡

የከተማው ገበያ በዋለበትና የኢሬቻ በዓል በተከበረበት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በርካታ ሕዝብ ተሰብስቦ ባለበት ከሁለት ሰዓት በላይ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ከሰባት በላይ ንጹሐን ዜጎች እንደተገደሉና ብዙዎችም እንደቆሰሉ፣ የዐይን እማኞች ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተዋል፡፡

አሁንም ሁለቱ ኀይሎች፣ በቅርብ ርቀት በፍጥጫ ላይ እንዳሉና ለደኅንነታቸውም ስጋት እንደገባቸው፣ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በየጊዜው በአካባቢው ያካሒዱታል ባሉትና የብዙ ንጹሐን ሕይወት እያለፈ ባለበት ግጭት እንደተማረሩ የገለጹት የቱሉ ምልኪ ነዋሪዎች፣ “ወይ በሰላም ይስማሙ አልያም ከመሀከላችን ገለል ብለው ቦታ እና ጊዜ መርጠው ይታኮሱ” ሲሉ መጨነቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከወራ ጃርሶ ወረዳ፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እና አስተዳደር ቢሮ፣ ከክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽንስ ቢሮ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

XS
SM
MD
LG