የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ /UN-OCHA/ በሱዳን ያለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ቅዠት በቅርብ ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ነው አለ።
በሱዳን ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም 9,000 ሰዎች ሞተዋል፣ ሌሎች 5.6 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ 25 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ድጋፍ ይሻሉ በማለት ድርጅቱ አስታውቋል። በተለይም በካርቱም በዳርፉር እና ኮርዶፋን ግዛቶች፤ ያለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የሆነ አደጋ እና ደም መፋሰስ ተካሂዷል፤ ሲል ያስታወቀው የድርጅቱ መግለጫ፤ በተለይም በዳርፉር አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊ ጥቃት እና በዘር የተነሳ የሚከሰቱ ግጭቶች መዘገባቸውንም አትቷል።
ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አንስቶም 45 የሚሆኑ የእርዳታ ሰራተኞች መገደላቸውን እና መታገታቸውን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድርጅቱ አክሎም መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተመናመኑ መሄዳቸውን፣ ከ70 በመቶ በላይ የጤና ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን እና እንዲሁም ደግሞ ሱዳንን ለመደገፍ ከሚያስፈልገው የ2.6 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 33 ከመቶ ብቻ መሟላቱን አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ እያሰጋት ሲሆን በገዳሪፍ፣ ካርቱም እና ኮርዶፋን ግዛቶች ከ1000 በላይ የበሽታው ምልከት የታየባቸው ግለሰቦች መኖራቸውንም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ /UN-OCHA/ በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ሃላፊነታቸውን ተረድተው በአለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ እንዲመሩ ጠይቋል። በተጨማሪም የሲቪሎችን ደህንነት ለመጠበቅ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን በጅዳ የገቡትን ቃል የሚጠብቁበት ጊዜ አሁን ነው ያለ ሲሆን አለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሱዳንን ህዝብ ቸል ሊል አይገባም ሲል አሳስባቧል።
መድረክ / ፎረም