በሳዑዲ አረቢያ፣ የእስር ጊዜያቸውን የጨረሱ ኢትዮጵያውያን፣ ወደ አገራቸው መመለስ ባለመቻላቸው፣ አሁንም በእስር ቤት ውስጥ ታጉረው ለከፍተኛ ሥቃይ እየተዳረጉ እንደኾኑ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ፡፡
ለደኅንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ኢትዮጵያውያን፣ በሳዑዲ እስር ቤቶች ከአንድ እስከ ዐሥር ዓመት ታስረው እንደቆዩና ቅጣታቸውን እንደጨረሱ ተናግረው፣ ኾኖም፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ አገራችን ሊመልሰን ባለመቻሉ፣ አሁንም ሽመይሲ በተባለው እስር ቤት ውስጥ ለልዩ ልዩ ችግሮች ተዳርገን እንገኛለን፤” ብለዋል፡፡
በቁጥር 300 የሚደርሱ ፍልሰተኞች፣ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተጠባበቁ እንዳሉ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አሁንም በሺመይሲ እስር ቤት ውስጥ፣ ከ50ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በሳዑዲ አረቢያ የእስር ጊዜያቸውን የጨረሱና በጊዜያዊ ማቆያዎች የሚገኙ ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን የማስመለስ ሥራ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር አስታውቆ፣ ፍርዳቸውን ያልጨረሱቱ ግን፣ በአገሪቱ ሕግ ብቻ እንደሚዳኙ አመልክቷል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።