የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድሩት የሃማስ ቡድኖች በቴል አቪቭ እና በዙሪያው በሚገኙ የእስራዔ ከተሞች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ በፈፀመች የዓየር ጥቃት ምክኒያት የምግብ የርዳታ ምግብ ማስተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት እንዲኾኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጥሪ አቀረበ።
ግጭቱ እየጠነከረ ከሄደ ለጦርነት ተጋላጭ የኾኑ ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሲቪሎች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ አቅርቦቶችን ለማግኘት ችግር እንደሚያጋጥማቸው፣ መቀመጫውን ሮም ያደረገው የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
ድርጅቱ ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ ለተጎዱት አካባቢዎች የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይደናቀፍ እና የምግብ አቅርቦት ማረጋገጥን ጨምሮ ሁሉም አካላት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን እንዲያከብሩ ጠይቋል።
"ተመድ በየወሩ 350 ሺሕ ለሚኾኑ ፍልስጤማውያን ቀጥተኛ የምግብ ርዳታ ይሰጣል ፣እንዲሁም ከሌሎች አጋሮች ጋራ በመተባበር ለሌሎች ወደ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ፍልስጤማውያን ርዳታ ያቀርባል" ያለው የድርጅቱ መግለጫ፣ አኹንም ለተፈናቀሉ ወይም በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ ዝግጁ መኾኑን አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም "ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሱቆች ሊኖራቸው የሚችለው ለአንድ ወር የሚበቃ የምግብ ክምችን ነው፣ ያም ቢኾን ጦርነቱ ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ሰዎች ያለውን ምግብ አብዝተው ሊሸምቱት ስለሚችሉ ክምችቱ በፍጥነት ሊሟጠጥ ይችላል" ብሏል። በተደጋጋሚ የኤሌትሪክ ሓይል መቆራረጥ ምክኒያትም ምግቦች ሊበላሹ እንደሚችሉ ድርጅቱ ስጋቱን አጋርቷል።
እሥራዔል እሁድ እለት ጋዛን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት ማድረሷን ቀጥላለች። እሥራዔል ጥቃቱን የጀመረችው፣ የሃማስ ተዋጊዎች እሥራዔልን ከጋዛ የሚለየውን አጥር ጥሰው በመግባት፣ ባለፉት አስርት ዓመታት ያልታየ ጥቃት በማድረሳቸው እና ከ700 በላይ ሰዎችን ገድለው በደርዘን የሚቆጠሩትን ደግሞ በማገታቸው ነው።
መሞታቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ውስጥ ሦስት እንግሊዛውያን፣ አንዲት ፈረንሳዊት እና ሁለት ዩክሬናውያን ሲገኙበት ጀርመን በሃማስ ከታገቱ ሰዎች ውስጥ ዜጎቿ እንደሚገኙበት አስታውቃለች።
መድረክ / ፎረም