በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ዓለምን እያስጨንቁ ካሉ ነገሮች አንዱ የመረጃ ፍሰት መዛባት ነው። ዐያሌ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ የብዙኀን መገናኛዎች፣ ለሐሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት እና ለመረጃዎች መባዛት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደኾነ ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ጋዜጠኛ ሰላም ተሾመ፣ የ“ያ ቴሌቪዥን” ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡ የመረጃ ፍሰት መዛባት፣ ለሐሰተኛ መረጃዎች ክፍተት በመተው፣ ማኅበረሰቡ በብዙኀን መገናኛዎች ላይ እምነት እንዲያጣ እያደረገው እንደኾነ አመልክታለች።
ሰላም በተለይ፣ መደበኛዎቹ የብሮድካስት እና የኅትመት ብዙኀን መገናኛዎች፣ ከመንግሥት እና ከተለያዩ ተቋማት የሚያገኟቸውን መረጃዎች፣ አንዳችም ሐቅን የማንጠር ሥራ ሳይሠሩ እንደወረዱ በማቅረብ፣ ከኹነቱ በሰዓታት እና በቀናት ልዩነት ዘግይተው በመዘገብ፣ ወገንተኝነት የሚታይባቸውን ግለሰቦች ሚዛናዊነት እና እርምት በጎደለው መልኩ የአየር ሰዓት በመስጠት እና በመሳሰሉት የተነሳ፣ ተኣማኒነታቸውን እያጡ መጥተዋል፤ ትላለች።
በብዙኀን መገናኛዎች ሥራቸውን አክበረው የሚያከናውኑ ባለሞያዎች፡- በሰው ሠራሽ ልህቀት የሚፈበረኩ መረጃዎችን የሚለዩባቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ፣ የሚጋብዟቸውን ባለሞያዎች ማንነት እንዲያውቁ፣ እንዲሁም መረጃዎችን በሰዓቱ እንዲያደርሱ፣ ምክረ ሐሳብ አንሥታለች።
በጥላቻ ንግግር እና በሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ላይ በተሳተፉ ብዙኀን መገናኛዎች ላይ፣ ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ፣ ለሌሎች መማሪያ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም አሳስባለች።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም